የጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ የትዊተር አካውንት ተጠለፈ

ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ትዊተር የጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ የትዊተር አካውንት መጠለፉን ይፋ አደረገ።

ይህ ተጠለፈ የተባለው የትዊተር ገጽ ከጠቅላይ ሚንስትሩ የግል ድረ-ገጽ ጋር ቁርኝነት ያለው ነው ተብሏል።

ትዊተር የጠቅላይ ሚንስትሩን አካውንት ከመረጃ መንታፊዎች እጅ አውጥቻለሁ ብሏል።

አካውንቱ ተጠልፎ በነበረበት ወቅት ሰዎች ክሪፕቶካረንሲዎችን በመጠቀም ለአቸኳይ እርዳታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ሲያቀርብ ነበር። ይህ ከሞዲ ድረ-ገጽ ጋር ግነኙነት አለው የተባለው አካውንት ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።

ከ61 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት የሞዲ የግል የትዊተር ገጽ ግን ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት ተገልጿል።

ትዊተር ስለጉዳዩ መረጃውን እንደደረሰው ተጠልፎ የነበረውን የትዊተር አካውንት ደህንነት ማረጋገጡን አስታውቋል።

የታዋዊ ሰዎች የትዊተር አካውንት ሲጠለፍ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በሐምሌ ወር የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እጩ ሆነው የቀረቡት ጆ ባይደን እንዲሁም የቴስላ መስራቹ ኤለን መስክ አካውንቶች ተጠልፈው ነበር።

ትዊተር ከሁለት ወራት በፊት የታዋቂ ግለሰቦች የሆኑ 130 አካውንቶች ላይ የሳይበር ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ ተደርጎ አንደነበረ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ በመረጃ መንታፊዎች ቁጥጥር ሥር የገቡት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አካውንቶች ብቻ ናቸው።

የጥቃቱ ኢላማ ከነበሩ ዝነኛ ሰዎች መካከል ባራክ ኦባማ፣ ኤለን መሰክ፣ ካንዬ ዌስት እና ቢል ጌትስ ተጠቃሽ ናቸው። ኤፍቢአይ ምርመራውን እንዲያከናውን ተጠይቆም ነበር።