ጆ ባይደን ጄኮብ ብሌክ ላይ የተኮሰው ፖሊስ እንዲከሰስ ጠየቁ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለፕሬዘዳንትነት የሚወዳደሩት የዴሞክራት እጩው ጆ ባይደን፤ ሁለት ጥቁር አሜሪካውያን ላይ የተኮሱ ፖሊሶች እንዲከሱ ጠየቁ።

ባይደን እንዲከሰሱ የጠየቁት ጄኮብ ብሌክ ላይ የተኮሰው ፖሊስ እና ብሬዎና ቴይለርን ተኩሰው የገደሉ ፖሊሶች ናቸው።

ዳልዌር ውስጥ ባደረጉት ንግግር፤ በክሱ ምን መካተት እንዳለበት ዝርዝር ነገር አልሰጡም።

የዴሞክራት እጩው ከነሐሴ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ አሰባስበዋል። ከምርጫው በፊት የተሠራ ዳሰሳ ከትራምፕ በተሻለ የመራጮች ድጋፍ እንዳላቸውም አሳይቷል።

ካምላ ሀሪስ ከዚህ ቀደም ጄኮብ ብሌክ እና ብሬዎና ቴይለር ላይ የተኮሱ ፖሊሶች እንዲከሰሱ ጠይቀው ነበር። ይህንን ይደግፉ እንደሆነ የተጠየቁት ባይደን “የፍትሕ ሂደቱ በራሱ መንገድ መሥራት አለበት። ፖሊሶቹ መከሰስ እንዳለባቸው አምናለሁ” ብለዋል።

ጄኮብ ሰባት ጊዜ ከጀርባው ፖሊስ ከተኮሰበት በኋላ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። እስካሁን የተኮሰው የፖሊስ አባል ላይ ግን እርምጃ አልተወሰደም።

የ26 ዓመቷ ብሬዎና ቤቷ ተኝታ ሳለች ፖሊሶች ተኩሰው እንደገደሏት ይታወሳል። አንድ ፖሊስ ከሥራ ሲሰናበት፤ ሁለት ሌሎች ፖሊሶች በጊዜያዊነት ታግደው ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል።

ፖርትላንድ ውስጥ የትራምፕ ደጋፊ ላይ የተኮሰና በሚዲያዎች ግራ ዘመም አቀንቃኝ የተባለውን ግለሰብ በተመለከተ ባይደን “ፍትሕ መገኘት አለበት” ብለዋል።

ጆ ባይደን ከጄኮብ አባት ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ትራምፕ ወደ ኪኖሻ ግዛት ሲሄዱ ከጄኮብ ቤተሰቦች ጋር አልተገናኙም።

ትራምፕ “ሕግ አልባ” ላሏቸው የኒው ዮርክ፣ ሲያትል፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና ፖርትላንድ ግዛቶች የፌደራል መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ ለማቋረጥ ሐሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ትራምፕ ይህን ባሉበት ቀን፤ ባይደን ነሐሴ ውስጥ 364 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰባቸውን ተናግረዋል። ይህም ፕራምፕ ካገኙት በላይ ነው።

የዴሞክራት እጩው ወደ 45 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ማስታወቂያ ያሠራሉ። የባይደን ተቀናቃኞች፤ ባይደን አመጸኞች ላይ እርምጃ አይወስድም ማለታቸውን ተከትሎ፤ ባይደን አቋማቸውን የሚያሳዩት በዚህ ማስታወቂያ ነው ተብሏል።