አሜሪካ ለኢትዮጵያ ‘ልትሰጥ የነበረውን 100 ሚሊዮን ዶላር ልትከለክል’ ነው

በሕዳሴ ግድበ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ ሕዳሴ ግድበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

በሕዳሴ ግድበ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ ሕዳሴ ግድበ

አሜሪካ በአጨቃጫቂው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለኢትዮጵያ ለመስጠት አቅዳ የነበረውን ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የእርዳታ ገንዘብ ልትከለክል መሆኑ ተነገረ።

አሜሪካ ከዚህ ውሳኔ የደረሰችው ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከት ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ከስምምነት ሳትደርስ የግድቡን ውሃ ሙሊት በማስጀመሯ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት ምንጭ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

“እስከ 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቅነሳ ሊደረግ ይችላል” ሲሉ የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ለሬውተርስ ተናግተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የግደቡ ደህንነት ሁኔታዎች ሳይጠኑ የውሃ ሙሌት መጀመር የለበትም የሚል አቋም ይዛ እንደነበረ ይህ የኮንግረስ አባል ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም 'ፎሬይን ፖሊሲ' የተባለው መጽሔትም አሜሪካ ለኢትዮጵያ ለመስጠት የመደበችውን 130 ሚሊዮን ዶላር ላለመስጠት መወሰኗን የውስጥ ምንጮቹን ጠቅሶ ከቀናት በፊት ዘግቦ ነበረ።

መጽሔቱ አሜሪካ ለደረሰችበት ለዚህ የእርዳታ ገንዘቡ እገዳ ውሳኔ ምክንያቱ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ካለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ እንደሆነ በዘገባው አስነብቧል።

በሌላ በኩል በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ፍጹም አረጋ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ልትሰጥ አቅዳው የነበረው የገንዘብ ድጋፍ እንዳይሰጥ የተደረገው "በጊዜያዊነት" ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር።

አምባሳደሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ላይ እንዳሰፈሩት የገንዘብ ድጋፉ የተያዘው ለአጭር ጊዜ መሆኑን ከሚመለከታቸው የአሜሪካ መንግሥት ኃላፊዎች እንደተረዱ ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ፍጹም አሜሪካ ለኢትዮጵያ የመደበችው 130 ሚሊዮን ዶላር እንዳይሰጥ መወሰኗ ከተሰማ በኋላ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ገልጸው የነበረ ሲሆን፤ በዚሁ መሰረት ነው ገንዘቡ በጊዜያዊነት እንዳይሰጥ መደረጉን እንደተረዱ ያመለከቱት።

ግብጽ የአባይ ውሃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል ስጋት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስትቃወም መቆይቷ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ግንባታው የአገሪቱ ዜጎች የሚፈልጉንት የኃይል መጠን ለማቅረብ የማደርገው ጥረት ነው ትላለች።

የሕዳሴ ግደብ ግንባታ ተጠናቆ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር እስከ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የአሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።