ዝነኛው ተዋናይ ዲዋይን እርሱና መላው ቤተሰቡ በኮቪድ-19 ተይዘው እንደነበር አስታወቀ

ዲዋይን

የፎቶው ባለመብት, Instagram

‘ዘ ሮክ’ በሚለው መጠሪያ የሚታወቀው ዝነኛው ተዋናይ ዲዋይን ጆንሰን እርሱን ጨምሮ መላው ቤተሰቡ በኮሮናቫይረስ ተይዘው እንደነበረ ይፋ አደረገ።

የቀድሞ የነጻ ትግል ስፖርተኛ እና የአሁኑ ከፍተኛ ገንዘብ ተከፋይ ተዋናዩ፤ የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን አጥብቀን ብንከተልም እኔን ጨምሮ ባለቤቴ እና ሁለት ሴት ልጆቼ በቫይረሱ ተይዘን ነበር ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ከቫይረሱ ማገገማቸውን እና ወደ ሌሎች ሰዎች ቫይረሱን እንደማናስተላልፍ ማወቃችን ትልቅ የአእምሮ እረፍት ሰጥቶናል ብሏል ዘ ሮክ።

የ48 ዓመቱ ጆንሰን እንዳለው፤ የ35 ዓመቷ ባለቤቱ ሎውራ፣ የ4 እና የ2 ዓመት ሴት ልጆቹ በቫይረሱ መያዛቸውን የተረዱት ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር።

ቫይረሱ “ከቅርብ የቤተሰብ አባል ጓደኞች” እንደያዛቸው የገለጸው ዘ ሮክ፤ የቤተሰብ አባላት ጓደኛ ያላቸው ሰዎችም በቫይረሱ ተይዘው እንደነበረ አላወቁም ብሏል።

“አንድ ልነግራችሁ የምችለው ነገር፤ ይህ እንደ ቤተሰብ ያሳለፍነው እጅግ በጣም ከባዱ ነገር ነው” ብሏል ተዋናዩ በኢንስታግራም ገጹ ላይ።

ከምንም ነገር በላይ ለቤተሰቤ ደህንነት ቅድሚያ እሰጣለሁ ያለው ዘ ሮክ ቫይረሱ በቤተሰብ አባላቱ ላይ ክፉ ጉዳት አለማስከተሉ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልጿል።

እንዳንድ ሰዎች እና ፖለቲከኞች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ እና ያለማደረግን ጉዳይ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሲያደርጉት ያስደንቀኛል ያለው ዲዋይን፤ “ጭምብል ማድረግ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ጭምብል አድርጉ። የበሽታውን ስርጭት ይቀንሳል። ይህ እውነታ ነው” ሲል በኢንታግራም ገጹ ላይ በለጠፈው ቪፊዮ ተናግሯል።