በአፍሪካ የተፈራውን ያክል ድህነት ሰዎችን ለኮሮናቫይረስ አጋልጧል?

ባልዲ ጭንቅላቷ ያደረገች ልጅ ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከአፍሪካ በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚዋ ደቡብ አፍሪካ ናት። አሁን ላይ ግን በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው።

በሌሎች የአፍሪካ አገራት ያለው ስርጭት መጠንም በአንጻራዊነት ዝግ ያለ ነው።

አፍሪካ ውስጥ በርካታ የተጨናነቁ መንደሮች አሉ። በእነዚህ መንደሮች ንጽህናና አካላዊ ርቀት መጠበቅ ከባድ ነው።

በአንጻራዊነት ደህና በሚባሉ ከተማ ቀመስ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ቫይረሱን በፍጥነት ሊያሰራጩት እንደሚችሉ የጤና ባለሙያዎች ሲያስጠነቅቁ ተደምጠዋል።

በደቡብ አፍሪካ የኮቪድ-19 አማካሪ ቡድን ኃላፊ ሳሊም አብዱል ካሪም እንደሚሉት፤ ሰዎች በብዛት፣ ተጨናንቀው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ቫይረሱ በፍጥነት ይሰራጫል።

እውነታው ከዚህ የባለሙያዎች መላ ምት ተቃራኒ ቢሆንስ? የተጨናነቁ መንደሮች እንደተገመተው ለበሽታው መሰራጨት ምክንያት ሳይሆኑ እንዲያውም ቫይረሱ በስፋት እንዳይስፋፋ አድርገው ቢሆንስ?

የአህጉሪቱ ድህነት እንደተፈራው ለወረርሽኙ ተጋላጭ ሳያደርጋት ቀርቶ ቢሆንስ?

ሚሥጥሩ ምንድን ነው?

ኮሮናቫይረስ መሰራጨት ሲጀምር ሁሉም ባለሙያዎች አፍሪካ አደጋ ውስጥ ትወድቃለች ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካው ቫይሮሎጂስት ሻቢር ማህዲ “ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደምንገባ አስቤ ነበር። አበቃልን ብዬም ነበር” ይላሉ።

በጣም ተስፋ ሰጪ ናቸው የተባሉ መላ ምቶች ሳይቀሩ ለህሙማን አልጋ እንደሚጠፋ፣ የጤና ሥርዓቱ እንደሚቃወስ ሲጠቁሙ ነበር።

ሆኖም ግን በደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዩናይትድ ኪንግደም በሰባት እጥፍ ያንሳል። ደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳትሆን ሌሎች አገራትም የተፈራው ያህል ቫይረሱ ጉዳት እያደረሰባቸው አይደለም።

ሆስፒታሎች እንደተሰጋው አልተጨናነቁም። በተቀረው ዓለም እንደተከሰተው የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ጫፍ ላይ ደርሶም አልታየም።

ፕ/ር ሻቢር፤ “በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የቫይረሱ ስርጭት ጫፍ አልታየም። ለምን እንደሆነ አልገባኝም። ግልጽ ያልሆነና ለማመን የሚያስቸግር ነው” ይላሉ።

አፍሪካ ውስጥ ኮሮናቫይረስ በአስጊ ሁኔታ ያልተሰራጨው አብዛኛው የአህጉሪቱ ነዋሪ ወጣት ስለሆነ ነው የሚሉ ባለሙያዎች አሉ።

የአፍሪካውያን አማካይ እድሜ ከአውሮፓውያኑ በግማሽ ያንሳል።

የቶኒ ብሌር ተቋም የአፍሪካ ዳይሬክተር ቲም ብሮምፊልድ እንደሚሉት፤ አፍሪካ የወጣቶች አህጉር መሆኗ ከበሽታው ተከላክሏታል።

ነገር ግን በበሽታው የተያዙ ሰዎችን እድሜ ከግምት ያስገቡ የስታትስቲክስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ እድሜ ከበሽታው የሚከላከል ብቸኛ ነገር አይደለም።

ፕ/ር ሳሊም “ትልቁ ነጥብ እድሜ አይደለም” የሚሉትም ለዚህ ነው።

በደቡብ አፍሪካ እና በሌሎችም አገራት ወረርሽኙ መሰራጨት እንደጀመረ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ ሚናው ቀላል አይደለም። ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉም ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።

በሌላ በኩል የአህጉሪቱ ከፍታ እና ሙቀት የበሽታውን ስርጭት ይቀንሳል የሚለው መላ ምት እንደማይሠራ ተገልጿል።

በቂ የመሠረተ ልማት ዝርጋት ባለመኖሩ ለወደፊት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው አሉ።

“አፍሪካ ክፉውን ጊዜ አልፋለች ማለት አልችልም። አንድ ቀን ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምር ይሆናል” ሲሉ ፕ/ር ሳሊም ያስረዳሉ።

ሌሎቹ ኮሮናቫይረሶች

በሶዌቶ የክትባት ቤተ ሙከራ ውስጥ ሳይንቲስቶች ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።

በቤተ ሙከራው ለአምስት ዓመታት የቆየ የሰው ደም ናሙና አለ። ይህም የኢንፍሉዌንዛ ክትባት ላይ ምርምር ሲካሄድ የተገኘ ናሙና ነው።

ተመራማሪዎቹ፤ ሰዎች በሌሎች አይነት ኮሮናቫይረሶች መያዛቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እየፈለጉ ነው። ይህ ማለት ሰውነት ራሱን ከኮቪድ-19 የሚከላከልበት አቅም አዳብሯል ማለት ነው።

“ከዚህ ቀደም በሽታን የመከላከል አቅም ማዳበር ተችሎ ሊሆን ይችላል። ቫይረሱ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የተስፋፋው ያህል በአፍሪካ ያልተሰራጨውም ለዚህ ይሆናል” ይላሉ ፕ/ር ሻቢር።

በተጨናነቀ መንደር የሚኖሩ ሰዎች ለቫይረሱ ተጋላጭ ስለሆኑ ምናልባትም በጊዜ ሂደት ኮቪድ-19ን መከላከል የሚያስችል አቅም አዳብረው ሊሆን እንደሚችል የደቡብ አፍሪካ ሳይንቲስቶች ይገምታሉ።

“በከፍተኛ ሁኔታ በተጨናነቁ አካባቢዎች በሽታውን የመከላከል አቅም ሊፈጠር ይችላል። ብዙ ሰዎች ምንም የበሽታው ምልክት የማይታይባቸው ወይም መጠነኛ ምልክት የሚያሳዩት ለዚህ ይሆናል” ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።

የአፍሪካ ድህነት የኮሮናቫይረስ ተጋላጭነትን ቀንሶት ሊሆን እንደሚችልም ያምናሉ።

በሌላ በኩል እንደ ብራዚል ባሉ ዜጎች ተጨናንቀው የሚኖሩባቸው አገሮች በርካቶች በቫይረሱ እየተያዙ ነው።