ኬንያ አል-ሸባብን በገንዘብ ይደግፋሉ ያለቻቸው ሰዎች ንብረት ላይ እገዳ ጣለች

አል-ሸባብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጽንፈኛውን ቡድን አል-ሸባብ በፋይናንስ ይደግፋሉ የተባሉ የ9 ሰዎች ንብረት እንዳይንቀሳቀስ የኬንያ መንግሥት እገዳ ጣለ።

የኬንያው የአገር ውስጥ ሚንስትር ይህ የመንግሥት ውሳኔ ኬንያ ‘የአገር ውስጥ ሽብርን’ ለመግታት ከወሰደቻቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ንብረታቸውን እንዳይንቀሳቀስ እገዳ የተጣለባቸው ዘጠኙ ግለሰቦች የኬንያ ዜጎች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የግለሰቦቹ ማንነትም ይሁን አሁን ስለሚገኙበት ሁኔታ የተባለ ነገር የለም።

ሚንስትሩ ፍሬድ ማቲአንጊ የዘጠኙ ግለሰቦች ንብረት ላይ እገዳ መጣሉ በኬንያ ሆነው አል-ሸባብን እንዳይደግፉ ያረጋል ብለዋል።

ሚንስትሩ ጨምረውም፤ መቀመጫውን ሶማሊያ ያደረገው አል-ሸባብ በኬንያ የሽብር ጥቃቶች ለመፈጸም ምለመላዎችን እያካሄደ እና በሲቪሉ ሕዝብ ውስጥ የራሱን ሰዎች አስርጎ እያስገባ ነው ብለዋል።

ይህ የኬንያ መንግሥት ውሳኔ የተሰማው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በኮቪድ-19 ምክንያት በቀጠናው የሽብር እንቅስቃሴዎች መጨመራቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ከሌሎች አገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ የሽብር እንቅስቃሴዎች፣ የስደተኞች ቁጥር እና የጦር መሣሪያ ዝውውር በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ባሉ አገራት ውስጥ ጭምሯል ብለዋል።

ኬንያ እአአ 2011 ላይ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ካዘመተች በኋላ በጽንፈኛው ቡድን በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመውባታል።

ከእነዚህም መካከል እአአ 2013 ላይ ዌስት ጌት ተብሎ በሚጠራው የገበያ ማዕከል ውስጥ አል-ሸባብ ባደረሰው ጥቃት ከ60 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል።

በቅርቡም በመዲናዋ በሚገኘው ቅንጡ ዱሲትዲ2 ሆቴል በአል-ሸባብ በተፈጸመ ጥቃት 21 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።