ስደተኞች ፡ ግሪክ መጠለያቸው የወደመባቸውን ስደተኞችን ለመርዳት ሦስት መርከቦችን ላከች

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ግሪክ በሌዝቦስ ደሴት የሚገኘው ትልቁ የስደተኞች ጣቢያ በእሳት መውደሙን ተከትሎ በየሜዳው የወደቁና መጠለያ አልባ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመርዳት ሦስት መርከቦችን እየላከች መሆኑ ተገለፀ።

ስደተኞቹ የሞሪያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያን ለቀው ከወጡ በኋላ ከነቤተሰባቸው በጎዳና፣ በሜዳ እና በመኪና ማቆሚያዎች ላይ መተኛት ከጀመሩ ሁለተኛ ቀናቸውን ይዘዋል።

በሞሪያ መጠለያ ጣቢያ 13 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ምቹ ባልሆነና በተጨናነቀ ሁኔታ ይኖሩበት ነበር። ማክሰኞ ምሽት የሞሪያ መጠለያ ጣቢያ በእሳት የተያያዘ ሲሆን ረቡዕ ዕለት ደግሞ የቀረው የስደተኞች ድንኳን በእሳቱ ወድሟል። 400 የሚጠጉ ታዳጊዎችና ህፃናትም አካባቢውን ለቀው ወደ ከተማ ተሰደዋል።

የግሪክ ባለሥልጣናት ለስደተኞቹ መጠለያ ለመስጠት ሁለት ጀልባዎችና መርከቦችን እየላኩ መሆናቸውን ገልፀዋል። የስደተኞች ሚኒስትር ኖቲስ ሚታራቺ፤ 2 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችም በጊዜያዊነት በመርከቦቹ ውስጥ እንዲጠለሉ ይደረጋሉ ብለዋል።

ነገር ግን ባለሥልጣናትም በወደመው በሞሪያ መጠለያ ጣቢያ ለነበሩት አስቸኳይ እርዳታ ለመስጠት እየሰሩ መሆናቸውንም አክለዋል።

በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን በርካታ ሚኒስትሮችም ሁኔታውን ለመመልከት ወደ ሥፍራው ተልከዋል።

የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪይሪያኮስ ሚሶታኪስ "በሞሪያ ያለው ሁኔታ በዚሁ ሊቀጥል አይችልም፤ ምክንያቱም የሕብረተሰብ ጤናም የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው" ብለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየንም "ቅድሚያ መሰጠት የሚገባው መጠለያ አልባ ለሆኑት ስደተኞች ነው" ብለዋል።

ሌዝቦስ ደሴት የሚገኘውን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የተነሳውን የእሳት አደጋ ለማጥፋት 25 የሚጠጉ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተረባርበዋል።

የዐይን እማኞች ሦስት ሰዎች በአደጋው መሞታቸውን ለቢቢሲ ቢናገሩም የግሪክ የስደተኞች ሚኒስትር "የጠፋ ሕይወትም ሆነ የተጎዳ የለም" ብለዋል።

አንዳንዶቹ በመጠለያ ጣቢያው አቅራቢያ ወደሚገኝና 3 ሺህ ሰዎችን መያዝ ወደሚችል ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ተመልሰዋል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ሚኒስትሩ አክለውም ባለፈው ሳምንት አንድ ስደተኛ በኮሮናቫይረስ መያዙን ተከትሎ በመጠለያ ጣቢያው የ15 ቀናት የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣሉ ውጥረት ነግሶ እንደነበር ተናግረዋል።

እሳቱ እንዴት እንደተጀመረ ግልፅ ባይሆንም አንዳንዶች ስደተኞችን ጥፋተኛ አድርገዋል፤ ሌሎች ደግሞ ግሪካውያን ናቸው ይህንን ያደረሱት ብለዋል።

ሞሪያ ለ13 ሺህ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሲሆን ከሚችለው በላይ በአራት እጥፍም ተጨናንቋል። ከነዚህ ስደተኞች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከአፍጋኒስታን ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከሰባ አገራት የመጡ እንደሆኑ ከኢንፎ ማይግራንትስ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።