በ2012 ጎልተው የወጡ ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ የብር ኖቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ወደ ስልጣን ያመጣው ለውጥ ይፋ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ከፖለቲካው በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችም እንደሚደረጉ ሲነገር ቆይቷል።

እነዚህን ማሻሻያዎች ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላሉ የተባሉ እርምጃዎች እየተጠናቀቀ ባለው 2012 የተወሰደ ሲሆን፤ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ግን ከተለያዩ ፈተናዎች አሁንም አልተላቀቀም።

በዓመቱ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ አለመረጋጋቶች፣ ዓለም አቀፉ የኮሮናወረርሽኝ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይና በሕዝቡ የዕለት ከዕለት ህይወት ላይ ቀላል የማይባል ጫናን አሳድረዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ገጽታ ላይ ጎልተው ከታዩ ጉዳዮች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እጠነከረ የመጣው የዋጋ ግሽበት፣ የብር የምንዛሪ ዋጋ በገበያ ይወሰናል መባል እንዲሁም የግል ባንኮች ከውጪ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ እንዲበደሩ መፈቀዱን መልስ ብለን ለመቃኘት እንሞክራለን።

የዋጋ ግሽበት

በአገሪቱ በተከታታይ ከፍ እያለ የመጣው የዋጋ ግሽበት ከመስከረም እስከ ሐምሌ 2012 ባሉት 11 ወራት ውስጥ የመቀነስ ምልክት እንዳልታየበት ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሚወጡት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለዋጋ ግሽበት መጠን አለመቀነስ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚቀመጠው በፍላጎት እና በአቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ መሆኑ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚስማሙበት ሃቅ ነው።

ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት መጠኑ በ18.6 በመቶ እና በ22.9 በመቶ መካከል ሲዋዥቅ ቆይቷል።

የምግብ ዋጋ ግሽበት ደግሞ ከ20 በመቶ ሳይወርድ ቆይቷል። ዝቅተኛ የምግብ ዋጋ ግሽበት የተመዘገበው በጥር 2012 ሲሆን የምግብ ግሽበት መጠኑም 20 በመቶ ነበር። መጋቢት 2012 ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ ዋጋ 26.7 በመቶ በመሆን በዓመቱ የምግብ ግሽበት ዋጋ ጣራ የነካበት ወቅት ወር ሆኖ አልፏል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበትም ቢሆን ባለፉት 11 ወራት ከ10.3 በመቶ እስከ 19.7 በመቶ መካከል ሆኖ ተመዝግቧል።

ከብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በተገኘው አሃዝ መሰረት ከመስከረም እስከ ሐምሌ 2012 ድረስ የተመዘገበው የምግብ የዋጋ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ እና አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት መጠኑ እንደሚከተለው ቀርቧል።

የብር የምንዛሪ ዋጋ በገበያ ይወሰን ስለመባሉ

ሌላ በዚህ ዓመት አነጋጋሪ ሆኖ ያለፈው ብሔራዊ ባንክ ከሦስት ዓመታት በኋላ የብር የምንዛሪ ዋጋ ተመን በገበያ ዋጋ ይወሰናል ማለቱ ነበር።

ባንኩ የብር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የብር ዋጋ በገበያ ተመን እንዲወሰን ማድረግ ተገቢ ነው በማለት ኢትዮጵያ በሦስት ዓመታት ውስጥ ብርን ወደ ፍሎቲንግ ካረንሲ ሥርዓት (የገንዘብን ተመን በገበያ ዋጋ ላይ መመስረት) እንደምትሸጋገር ሐምሌ ወር ማገባደጃ ላይ ገልጿል።

ብር በአሁኑ ወቅት ከሚገባው በላይ ዋጋ እንዳለው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ስለዚህም የብር ዋጋ በገበያ ወደሚተመንበት ሥርዓት ሲሸጋገር ዋጋው አሁን ካለው እንደሚቀንስ ወይም በብር እና በዶላር መካከል ያለው ልዩነት እንደሚሰፋ ይታመናል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የምንዛሪ ሥርዓት በገበያ ዋጋ መወሰን እንዳለበት ይሚስማሙበት ጉዳይ ሆኖ፤ አካሄዱ ግን ቀስ በቀስ መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።

ብሔራዊ ባንክም በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ መከናወን ያለባቸው ነገሮችን መሰራት እንደሚኖርበትና ለዚህ ደግሞ የዘርፉ ሙያተኞችን የያዘ ተቋም ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

የብር የዋጋ በገበያው መሠረት ሲተመን ከውጭ አገራት ገንዘብ ጋር የሚኖረው ልዩነት እንደሚሰፋ ሙያተኞች ይናገራሉ፤ ለምሳሌ አንድ የአሜሪካ ዶላር ዛሬ ላይ በባንኮች 35 ብር የሚመነዘር ከሆነ፤ በትክክለኛው የገበያ ዋጋ ይተመን ቢባል አንድ ዶላር እስከ 45 ብር ድረስ ሊመነዘር ይችላል። ይህም የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል።

በሌላ በኩል ብር በአሁኑ ወቅት ከሚገባው በላይ ዋጋ እንዳለው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ስለዚህም የብር ዋጋ በገበያ ወደሚተመንበት ሥርዓት ሲሸጋገር ዋጋው አሁን ካለው እንደሚቀንስ ወይም በብር እና በዶላር መካከል ያለው ልዩነት እንደሚሰፋ ይታመናል።

በዚህም ኢትዮጵያ የምታመርታው ምርት ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ርካሽ ይሆናል፤ ይህም የአገር ውስጥ አምራቾችን ተወዳዳሪ እንደሚያደርግ በመጥቀስ መልካም አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

ባንኮች በው ምንዛ እንዲበደሩ መፈቀዱ

ብሔራዊ ባንክ ከሳምንታት በፊት ይፋ ካደረጋቸው መመሪያዎች መካከል የግል ባንኮች በራሳቸው ጊዜ በውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ይበደሩ የሚለው ይገኝበታል።

ይህ የባንኩ ውሳኔ ኢትዮጵያ ጥብቅ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደሯን እያላላች ስለመምጣቷ የሚያመላክት ሲሆን፤ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ ከአገር ውጭ እንዲበደሩ መፍቀዱ ለላኪዎች መልካም አጋጣሚን ይዞ የሚመጣ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲጎለብትም ይህ ውሳኔ ከፍተኛ አስተጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።

የውጭ ኢንቨስተሮች በአንድ አገር ኢንቨስት ለማድረግ ከመሰናቸው በፊት ኢንቨስት በሚያደርጉበት አገር ግብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት እንዲሁም ትርፋቸውን ይዘው ለመውጣት በቂ የውጪ ምንዛሬ መኖሩን ቀድመው ያረጋግጣሉ።

ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ባለባት ኢትዮጵያ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ መኖሩ ምልካም አጋጣሚ እንደሚሆን በአንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይታመናል።

በሌላ በኩል ደግሞ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ የሚበደሩትን ገንዘብ ከእነ ወለዱ በውጭ ምንዛሪ እንደመመለሳቸው የምንዛሪ ተመን መዋዠቅ በአገር ውስጥ ባንኮች ላይ አሉታዊ ጫና ሊፈጥር ይችላል።