ጾታዊ ጥቃት፡ ለሴቶች ከለላ መሆን የምታስበው "ከለላ"

የከለላ ለልጆች ዲዛይን

የፎቶው ባለመብት, Kelela

ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ሰላም ሙሴና ሁለት ጓደኞቿ አንድ የእረፍት ቀናቸውን ቡና እየጠጡ ለማሳለፍ ተገናኙ። ቀጠሯቸው ሁሌም በሚያዘወትሩት ካፌ ውስጥ ነበር።

ወሬን ወሬ እያነሳው ስለፍቅር ሕይወታቸው መነጋገር ጀመሩ። አንድ ጓደኛዋ ከልጅነቷ ጀምሮ በግቢያቸው ውስጥ የሚኖሩ ወንዶች የተለያዩ ጾታዊ ትንኮሳዎች ያደርሱባት እንደነበር ድንገት በወሬያቸው መካከል ጣል አደረገች።

ከዚህ በኋላ ግን የወሬው ርዕሰ ጉዳይ ተለወጠ። ወሬው የነበረው ግለትም ውሃ ተቸለሰበት። በሳቅና በወዳጅነት ስሜት ታጅቦ የነበረው ጨዋታ ውስጥ የሃፍረትና የመሸማቀቅ ነፋስ ገባ።

ይህንን ማየት ለሰላም ግርምታን ፈጥሯል። ዘወትር ስለሴቶች ጥቃት፣ እኩልነት የምታወራዋ ጓደኛዋ በእርሷ ላይ ስለደረሰው ትንኮሳ ማውራት ማፈሯ ትኩረቷን ሳበው።

ከጓደኞቿ ጋር ተለያይታ ወደ ቤቷ ካመራች በኋላ ከሌላኛዋ ጓደኛዋ መልዕክት በስልኳ ደረሳት። ጓደኛዋ በአጎቷ/በአክስቷ ልጅ በተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን አስተናግዳለች።

ቅርብ ላለችው የቤተሰቧ አባል ብትናገርም እርሷን ከሃፍረትና ከመሸማቀቅ የሚያድናት አልሆነም።

ለሰላም ይህንን መስማቷ በርካታ ጥያቄዎችን እንድታስተናግድ አደረጋት። ምን ያህል ሴቶች በልጅነታቸው ትንኮሳን፣ ጥቃትን አስተናግደዋል? ምን ያህል ሰዎች ጥቃት ወይንም ትንኮሳ መድረሱን ሰምተው ምንም ሳያደርጉ ቀርተዋል?

ይህንን የጓደኞቿን ታሪክ አስፈቅዳ በፌስቡክ ሰሌዳዋ ላይ ካጋራች በኋላ በርካቶች በግሏ መልዕክት ላኩላት።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እርሷና ጓደኞቿ አንድ ነገር ለማድረግ ተሰባሰቡ።

ጾታዊ ጥቃት ለሚደርስባቸው ከለላ ለመሆን በማሰባቸው ለቡድናው 'ከለላ' በማለት ስም አወጡለት።

እነሆ ከለላ ለልጆች፤ ከሦስት ዓመት በኋላ ለተጠቃሚዎች በማህበራዊ ድረ ገጾችና፣ በድረ ገጽ በኩል ደረሰ።

ጥቃት ከሩቅ አይመጣም

ኅብረተሰቡ ብዙ ጊዜ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች ከሩቅ የሚመጡ እንደሆኑ ያስባል ትላለች ሰላም ሙሴ።

በቴሌቪዥን በሬዲዮ በሚታዩ ድራማዎች፣ በመጽሐፍት ተደርሰው የምናነባቸው ታሪኮችም ላይ የምናስተውለው ጥቃት አድራሾች ከውጪ መጥተው እንደሆነ ነው።

ከዚህ እንኳ ቢያልፍ በማኅበረሰቡ ውስጥ ቅቡልነት በሌላቸው፣ እንደ ክፉ በሚታዩና በሚቆጠሩ ሰዎች ጥቃት እንደሚደርስ ተስለው እናነባለን፤ እናያለን።

እውነታው ግን ከዚያ የራቀ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ጾታዊ እንዲሁም የወሲብ ጥቃት በልጆች እንዲሁም በአዋቂዎች ላይ የሚፈፀመው በሚታወቁና ቅርብ በሆኑ ሰዎች መሆኑን ሰላም ትናገራለች።

በተለይ ሕጻናት ለጥቃት የሚጋለጡት በተከራዮች፣ በቤተሰብ አባላት፣ በዘመዶች መሆኑን በማንሳት ይህ ጉዳይ ጥቃቶች ተዳፍነው እንዲቀሩ እንደሚያደርግ ታነሳለች።

"በይበልጥ ደግሞ አለመወራቱ፣ ችግሩ እንደሌለ አድርጎ እንዲሰማን ያደርጋል" ስትል ታብራራለች።

በልጅነት እድሜ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጠር፣ ጥቃት አድራሾች የሚያደርሱት ማስፈራሪያ፣ ለሌላ ሰው እንዳይናገሩ የሚፈጥሩት ማሳመኛ፣ ጥቃቶቹ ሳይነገሩ እንዲቀሩ መሆናቸው ትገልጻለች።

"በባህላችንም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች የማውራት ነጻነቱ ስለሌለ፣ ልጆች ለእንዲህ አይነት ጥቃቶች ቋንቋ የላቸውም" የምትለው ሰላም፤ "እከሌ እኮ እንደዚህ አደረገኝ፤ እንደዚህ ዓይነት ቦታ ላይ እንዲህ አደረገኝ፤ እንደዚህ ነካኝ" ለማለት ቋንቋ እንደሚቸግራቸው ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Kelela

ወላጆች አሳዳጊዎች እንዲሁም መምህራንም እነዚህን ጥቃቶች አብራርተው ለማስረዳት የሚያስችላቸው ቋንቋ አለመጎልበቱን ታነሳለች።

ይህ ብቻም ሳይሆን በምን መልኩ እናስተምራቸው ለሚለው የሚረዳ መሳሪያ፣ መምሪያ አለመኖሩን ሰላም ትጠቅሳለች።

እነዚህ ክፍተቶች መኖራቸው ልጆቹ ጥቃት በደረሰባቸው ወቅት ሄደው እንዳይናገሩ እንደሚያደርጋቸው፣ የልጆች ነገር ያሳስበኛል የሚሉ አካላት፣ ወላጆች አሳዳጊዎችና መምህራን እነዚህን ጉዳዮች ለማስተማር ጥቃቱን ለመካከል ቀድሞ ለማስተማር የሚያስችላቸው መንገድ ያጣሉ።

ብዙ ጊዜ ጥቃቱ ሲፈፀም ልጆች የሚያሳይዋቸው ምልክቶች ይኖራሉ የምትለው ሰላም፣ ነገር ግን ስለ ምልክቶቹ የቀደመ እውቀት የሌለው ሰው ልጆቹ ላይ ስለደረሰው ነገር ተረድቶ ለመደገፍና እርምጃ ለመውሰድ ይቸገራል ትላለች።

ስለዚህ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በማለት "ከለላ" መዘጋጀቱን ለቢቢሲ ገልፃለች።

"ከለላ የበይነ መረብ መድረክ ነች" የሚለው ሃሳብ የሰፈረው በማኅበራዊ ድረ ገፁ ሰሌዳ ላይ ነው።

'ከለላ' ለዚህ መልስ አለው?

በ2010 ዓ.ም በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተሰባስበው፣ ስር የሰደዱ ማኅበረሰባዊ ችግሮችን ለመዋጋት የሚረዱ ሃሳቦችና መሳሪያዎች በበይነ መድረክ ለማዘጋጀት በአንድ ሃሳብ ፀኑ።

እነዚህ በጎ ፈቃደኞች የመጀመሪያ የሆነችውን ስራቸውን፣ ከለላ ለልጆች፣ በቀላል ቋንቋ፣ ለቤተሰቦች፣ ለሕግ ባለሙያዎች፣ ለአሳዳጊዎችና መምህራን በሚሆን መልኩ ለማዘጋጀት ስራ ጀመሩ።

በጎ ፈቃደኞቹ የሥነ አእምሮ፣ የሥነልቦና፣ የሕግ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን መምርያውን መጻፋቸውን ሰላም ትገልጻለች።።

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው እነዚህ ሙያዎችን ነው የምትለው ሰላም፤ ሥራው ሁለት ዓመት የፈጀውም የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ በመሆኑ ነው።

"ከለላ" ለልጆች መምሪያን በከለላ ድረገጽ፣ በቴሌግራም፣ ፌስቡክና ትዊተር ማግኘት እንደሚቻል የምትናገረው ሰላም እስካሁን ታትሞ መሰራጨት አለመጀመሩን ነግራናለች።

መምሪያው በማኅበራዊ ድረገጾችና በድረገጽ ላይ እንዲሰራጭ ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን አሳትሞ ለማሰራጨት ለሚፈልጉ ዝግጁ ነው።

ከለላ ዓላማ አድርጋ የተነሳችው በማኅበረሰቡ ውስጥ ስር የሰደዱ ማኅበረሰባዊ ችግሮችን ለመዋጋትና፣ እነዚህን ችግሮች የሚያስቀጥሉና የሚያባብሱ ሥርዓቶችን ማስወገድ ነው።

በዚያውም ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃትን እንዲሁም የሴቶች እኩልነት ጨምሮ ግንዛቤ ለመፍጠር እና መዋቅራዊ የሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራት መሰባሰባቸውን ሰላም ትናገራለች።

ከለላ ለልጆች፤ ከለላ ካዘጋጃቸው መሳሪያዎች መካከል ልጆች ላይ ከሚደርስ ጥቃት ጋር በተያያዘ መምሪያ ሆኖ የቀረበ እና የመጀመሪያ ሥራቸው መሆኑን የምትጠቅሰው ሰላም፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ ሌሎች መምሪያዎችም ሆኑ በራሪ ወረቀቶች ሊያዘጋጁ አንደሚችሉ ገልጻለች።

ከለላ በትግርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዘኛ የወጣ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላም በአፋርኛ እና ሶማልኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁት መምሪያዎች እንደሚወጡ ሰላም ለቢቢሲ ተናግራለች።

እነዚህ በአገር ውስጥ ቋንቋ የተዘጋጁ መምሪያዎች ማንበብ ለሚችሉ የተዘጋጁ ናቸው። ማንበብ ለማይችሉ ደግሞ በሚደመጥ መልኩ ለማዳረስ እየተዘጋጁ ናቸው ተብሏል።

ከለላ ለልጆችን በተለያየ ይዘት እና መልክ ተዘጋጅታ ለተለያየ ሕብረተሰብ አካላት ለማዳረስ አቅደው እየሰሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ፤ ለወደፊት ከሴቶች እኩልነት፣ ከጾታዊ ጥቃት ጋር የተገናኙ ይዘቶችን አደራጅቶ ለማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ለቢቢሲ ገልጻለች።

ከለላ ለልጆች ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች በተጨማሪ በእንግሊዘኛ ማዘጋጀት ያስፈለገበትን ምክንያት ሰላም ስታስረዳ፤ በኬንያ፣ አንጎላ እና ደቡብ አፍሪካ ላይ መምሪያውን ለመጠቀም ፍላጎት በመኖሩ መሆኑን ታነሳለች።

ከለላ ለልጆችን በየአገራቱ አውድ ተርጉሞ ለማቅረብ ፍላጎት በመኖሩ በእንግሊዘኛ ለማዘጋጀታቸው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሳለች።

ከለላ በውስጧ ምን ይዛለች?

ከለላ በአጠቃላይ ስለልጆች ወሲባዊ ጥቃት ምንነት፣ አጥቂዎች እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉና፣ ልጆች ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ሊያሳይዋቸው ስለሚችሏቸው ምልክቶች ዝርዝር ጉዳዮችን ይዛለች።

እንዲሁም ጥቃትን እንዴት መከላከል እንደሚቻል በመግለጽ፣ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ደግሞ ምን መደረግ አለበት የሚለውን በሰፊው ታብራራለች።

ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት በደረሰም ወቅት ሕክምና እና የሕግ አገልግሎት የሚገኝባቸውን አድራሻዎችን አካትታለች።

ከለላ በተሰኘው መምሪያ ላይ የሕግ ክፍሎቹን በመጻፍ የተሳተፈችው የሕግ ባለሙያዋ አክሊል ሰለሞን በበኩሏ መምሪያው የያዘው የሕግ ጉዳይ በዋናነት እንዲያተኩር የፈለጉት ተጠቂዎች ማወቅ የሚገባቸውን የሕግ አካሄድ ነጥቦች ለማሳወቅ መሆኑን ትናገራለች።

በመምሪያው ላይ ጥቃት ከደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና መረጃ የሚወሰደው እንዴት ነው? ማን ነው የሚወስደው፣ የት ነው የሚወሰደው የሚሉት ጉዳዮች በዚህ ክፍል መዳሰሳቸውን ትገልጻለች።

አንድ ጥቃት ሲፈፀም የወንጀል ሥርዓቱ ላይ ምን ይመስላል የሚለውን ከምርመራ አንስቶ እስከ የፍርድ ውሳኔ አስኪሰጥ ድረስ ያለው ሂደት በሰነዱ ውስጥ ማካተታቸውን ትናገራለች።

ጥቃት ከደረሰባቸው ሕጻናት መረጃ ሲሰበሰብ ምን መደረግ አለበት፣ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ምን ማድረግ አለባቸው፣ የሚለው በመምሪያው ላይ መካተቱን የገለፀችው የሕግ ባለሙያዋ፣ ከአጥቂው ጋር መገናኘት እንደሌለባቸው፣ የሥነልቦና ድጋፍ ማግኘት መብታቸው መሆኑንና እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች መጠቀሳቸውን ገልጻለች።

የሕግ ባለሙያዋ አክላም ጥቃት ደርሶ ጥቆማ በሚሰጥበት ወቅት ወላጆች ወይንም አሳዳጊዎች አብረው እንዲሆኑ፣ የሥነልቦና ባለሙያ አብሯቸው እንዲገኝ፤ እንዲሁም የጥያቄው አካሄድ የማይመቻቸው አልያም ለበለጠ ጭንቀትና መረበሽ የሚያጋልጣቸው ከሆነ ማስቆም እንደሚችሉ በመመሪያው ላይ ተቀምጧል ስትል ታብራራለች።

አክላም ጥቃት አድራሹ ወላጅ ወይንም አሳዳጊ ከሆነ ደግሞ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው መካተቱን ታስረዳለች።

ተጠቃሚዎች በሕግ ሥርዓቱ ላይ ግራ የሚያጋባቸው ነገር ካለ በከለላ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ፣ በዚያም ምላሽ እንደሚሰጡ ገልፃለች።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

"በሀገራችን ከሶስት ሴቶች አንዷ ላይ ጾታዊ ጥቃት ይደርሳል"