በግሪከ ትልቁ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በእሳት ተቃጠለ

በግሪክ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የተነሳው እሳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በግሪክ፣ ሌዝቦስ ደሴት የሚገኘው ትልቁ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በእሳት ተቃጥሏል። ሞሪያ ተብሎ የሚጠራው ይህ ጣቢያ በስደተኞች የተጨናነቀ ነው።

25 የሚጠጉ የእሳት አደጋ ሰራተኞችም እሳቱን ለማጥፋት ተረባርበዋል።

በርካታ ስደተኞች እሳቱ ሳይነካቸው መውጣት ቢችሉም አንዳንዶች በአደጋው ተጎድተዋል ተብሏል።

እሳቱ እንዴት እንደተጀመረ ግልፅ ባይሆንም አንዳንዶች ስደተኞችን ጥፋተኛ አድርገዋል፤ ሌሎች ደግሞ ግሪካውያን ናቸው ይህንን ያደረሱት ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ከጣቢያው ወደ ሌሎች ከተሞች የሚወስዱ መንገዶችን ፖሊስ የዘጋ ሲሆን ይህም ስደተኞች ወደ ሌሎች ከተሞች እንዳያቀኑም ለመከላከል ነው ተብሏል።

በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ያለመጠለያ ተቸግረው እንዳሉም ተገልጿል። ባለስልጣናቱም መጠለያ ለማግኘት ፈታኝ ሆኖባቸዋል።

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄይኮ የእሳት አደጋውን "የሰብዓዊ ቀውስ" በማለት የጠሩት ሲሆን ስደተኞቹንም ፈቃደኛ ለሆኑ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራትም እንዲወስዷቸው በትዊተር ገፃቸው ጥሪ አድርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ስደተኞች ከእሳቱ ሲሸሹ

ስደተኞቹ እሳቱን በማምለጥ አቅራቢያቸው ወዳሉ ከተሞችም ሲሸሹ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃት አድርሰውባቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር)ና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ በጣቢያው አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ነዋሪዎችና ስደተኞች መካከል ያለው ውጥረት እንደሚያውቁት በመግለጫቸው አትተዋል።

"ሁሉም አካላት ምንም አይነት ነገር ከመፈፀም እንዲቆጠቡ" ጥሪ ያደረገው መግለጫው ስደተኞቹም እንቅስቃሴያቸውን በመገደብ መጠለያ እስኪገኝም ድረስ በጣቢያው አቅራቢያ ተሰብሰቡ ተብሏል።

ሞሪያ ለ13 ሺህ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሲሆን ከሚችለው በላይ በአራት እጥፍም ተጨናንቋል። ከነዚህ ስደተኞች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከአፍጋኒስታን ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከሰባ አገራት የመጡ እንደሆኑ ከኢንፎ ማይግራንትስ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ሞሪያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በእሳት ከተያያዘ በኋላ