የትግራይ ምርጫ፡ "ይህንን ምርጫ እንደ ሪፈረንደም ነው የምናየው" የትግራይ ተቃዋሚ ድርጅት

ትግራይ ትመርጣለች የሚል አርማ

በዛሬው ዕለት በትግራይ ክልል ክልላዊ ምርጫ እየተካሄደ ሲሆን መራጮች ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምፃቸውን ሲሰጡ ውለዋል።

በክልላዊ ምርጫው ክልሉን የሚያስተዳድረውን ህወሓትን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች እየተሳተፉም ይገኛሉ።

ድርጅታቸውን በመወከል እየተፎካከሩ ያሉት የሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና ውናት (ውድብ ነፃነት ትግራይ) የተቃዋሚ አመራሮች በመቐለ ከተማ ድምፅ ሰጥተዋል።

ትግራይ ነፃ አገር ሆና ልትመሰረት ይገባል በማለት የሚያቀነቅነው የውናት ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳኦች ሃላፊ መሃሪ ዮሃንስ ምርጫው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር ፉክክር በላይ ትርጉም ያለው እንደሆነም ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ይህች ቀን የትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ በተግባር ያረጋገጠበት ሰለሆነች የተለየች ናት" ብሏል።

"እንደ ውናት ይህንን ምርጫ እንደ ሪፈረንደም ነው የምናየው። እንደ ሕዝብ ትልቅ ዋጋ የከፈለበት መብት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ከእዚህም አደጋ ወጥቶ የሉአላዊነትና የግዛት ነፃነት የሚያረጋግጥበት ሁኔታ መፈጠር አለበት" በማለት "ማስፈራርያ ቢመጣም እሱን ተቋቁመን እዚሁ ደርሰናል" በማለት ተናግሯል።

ሌላኛው በከተማዋ ድምፁን የሰጠው የባይቶና ሊቀመንበር ኪዳነ አመነ በምርጫው ሂደት በበኩሉ ደስተኛ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል::

መራጩ አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ፣ የፀረ-ተህዋሲያን (ሳኒታይዘር) በርካቶች ይዘውና በመጠቀም በአግባቡ ሲመርጡ መታዘቡን ተናግሯል።

የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ኃያሉ ጎድፋይም በደቡብ ትግራይ አላጀ ወረዳ ከሌሎች አራት የድርጅቱ አመራሮች ጋር ሆኖ ቦራ በተባለ የድምፅ መስጫ ጣቢያ ላይ ድምፅ መስጠቱን ተናገሯል።

"በጣም ደስ ብሎኛል። ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ምርጫው እንዳይደናቀፍ የራሱ አስተዋፅኦ አድርጓል። ስለዚህ ይህቺ ቀን ለእኛ የተለየ ትርጉም ነው ያላት:: ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ከተጠናቀቀ ድግሞ የበለጠ ሙሉ ትርጉም ይኖረዋል" ብሏል።

ምንም እንኳን በምርጫው ከሞላ ጎደል ደስተኛ ቢሆኑም አንዳንድ ቅሬታ እንዳላቸውና አጠቃለው መግለጫ እንደሚሰጡበት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በክልሉ 2 ሺህ 672 የምርጫ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን መቀለ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት ከንጋት 10፡30 ጀምሮ ምርጫ ጣቢያዎች ፊት ለፊት ተሰልፈው መመልከቱን ገልጿል።

በክልሉ 38 የምርጫ ክልሎች እንዳሉ የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ በነሐሴ መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ከተላለፈ በኋላ፤ በትግራይ በተናጠል እየተካሄደ የሚገኘው ክልላዊ ምርጫ ሕገ-ወጥና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት የፌደሬሽን ምክር ቤት መወሰኑ ይታወሳል።