ደቡብ አፍሪካ፡ የኔልሰን ማንዴላ ጠበቃ ጆርጅ ቢዞ አረፉ

ጆርጅ ቢዞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኔልሰን ማንዴላ ጠበቃ የነበሩትና ስመ ጥሩው የሰብዓዊ መብት የህግ ባለሙያ ጆርጅ ቢዞ በ92 አመታቸው አረፉ።

ደቡብ አፍሪካውያን ከጨቋኙ አፓርታይድ ግዛት ነፃ ለመውጣት በሚያደርጉት ትግል ለታሰሩ የነፃነት ታጎዮችም ጥብቅና ቆመዋል።

ከዚህም በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካን ህገ መንግሥትም በማርቀቅ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራሞፎሳ ሞታቸውን ባወጁበት ሰዓት ጆርጅ ቢዞ "ለአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል" ብለዋል።

በቀድሞው የነፃነት ታጋይና የአገሪቱ መሪ የተሰየመው የኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽንም "በደቡብ አፍሪካ ታሪክ ትልቅ ስም ያላቸውና በአለም ፍትህ እንዲሰፍን የታገሉት አለፉ" ብሏል

ግለሰቡ በተፈጥሯዊ ሞት እንደሞቱም ቤተሰቦቻቸው ገልፀዋል።

ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንዴት ይታያል?

ጆርጅ ቢዞ ለበርካታ ሰዎች ጥብቅና ቢቆሙም ብዙዎች ከኔልሰን ማንዴላ ጋር አብረው ያነሷቸዋል።

ጆርጅ ቢዞና ማንዴላ የተዋወቁት ጆሃንስበርግ የህግ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት ነው።

ማንዴላ ለእስር ከበቁ በኋላም እሳቸውን ጨምሮ ስመ ጥር ለሚባሉ የፀረ- አፓርታይድ ታጋዮች በጥብቅና ቆመዋል።

በጎርጎሳውያኑ 1956 አገር በመካድ ወንጀል ተወንጅለው ኔልሰን ማንዴላ ፍርድ ቤት በቆሙበት ወቅት ጆርጅ ቢዞ የህግ ባለሙያቸው ነበሩ።

ከዚህም በተጨማሪ ማንዴላና ሌሎች የነፃነት ታጋዮች የአፓርታይድን መንግሥት ለመጣል አሲረዋል ተብለው በጎርጎሳውያኑ 1964 የእድሜ ልክ ሲበየንባቸውም ጆርጅ ቢዞ ነበሩ።

ማንዴላ በእስር በነበሩበትም ወቅት ከጎናቸው የነበበሩ የህግ ባለሙያ ነበሩ። ማንዴላ የግል ታሪካቸውን ባሰፈሩበት "ሎንግ ዋክ ቱ ፍሪደም' መፅሃፋቸውም ጆርጅ ቢዞ "አዛኝ፣ ሩህሩህና ጎበዝ ሰው ነበር"ብለውታል።

ከማንዴላም ጋር በመጨረሻ ህይወታቸውም ዘመን ጠበቅ ያለ ጓደኝነት እንደነበራቸውም ፋውንዴሽኑ አስታውሷል።

ጆርጅ ቢዞ የተወለዱት ግሪክ ሲሆን ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡትም በሁለተኛው አለም ጦርነት ተሰደው በ13 አመታቸው ነው።

ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመምጣታቸውም በፊት ከአባታቸው ጋር ሆነው በናዚ ቁጥጥር በነበረችው ግሪክ ውስጥ ምርኮኛ የነበሩ ሰባት የኒውዚላንድ ወታደሮችን እንዲያመልጡ ረድተዋል።

ጆሃንስበርግ ከመጡ በኋላ በአንድ የግሪክ ሱቅ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር። በኋላም ትምህርታቸውን በዊትዋተርስትራንድ ዩኒቨርስቲ በህግ ተመርቀዋል።

ጆርጅ ቢዞ ካበረከቷቸው በርካታ ስራዎች መካከል ከስምንት አመታት በፊት በፖሊስ የተገደሉ 34 የማዕድን ሰራተኞች ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈላቸው ማድረጋቸውም የሚጠቀስ ነው።