ኮሮናቫይረስ፡ የኮሮና ክትባትን በዓለም ለማሰራጨት 8ሺህ ግዙፍ አውሮፕላኖች ያስፈልጋሉ

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይበለውና የኮሮና ክትባት ቢሳካ በነገታው እንወጋዋለን ማለት አይደለም፡፡ በመላው ዓለም ማሰራጨቱ በራሱ ሌላ ትልቅ ፈተና ነው ሲል የአቪየሽን ኢንደስትሪ ማኅበር ተናግሯል፡፡

ምናልባትም በአውሮፕላን የካርጎ ታሪክ እጅግ ከባዱ ፈተና፣ እጅግ ከባዱ ኃላፊነት ይሆናል ተብሏል፡፡

የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) እንደሚለው ምናልባት ክትባቱ ቢሳካ እያንዳንዳቸው የቦይንግ 747 አውሮፕላኖች አይነት ግዝፈትና ፍጥነት ያላቸው 8ሺህ ግዙፍ የካርጎ አውሮፕላኖች ያስፈልጋሉ ብሏል፤ ክትባቱን ለማዳረስ፡፡

ምንም እንኳ ለጊዜው ክትባት ባይፈበረክም፣ መሳካቱ አይቀርም በሚል የአየር ትራንስፖርት ማኅበሩ ነገሮችን ለማቀናጀት ከወዲሁ ተፍ ተፍ እያለ ነው፡፡

ማኅበሩ በጤና ዙርያ ከሚሰሩት በርካታ ድርጅቶች፣ ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከመድኃኒት አምራቾች፣ ከመድኃኒት አቀባባዮች፣ አከፋፋዮች፣ ከአውሮፕላን ካርጎ ሥራ ተሳታፊዎች ጋር በጥምረት መስራት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ይህ 8ሺህ ቦይንግ ያስፈልጋል የተባለው ታዲያ አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ ብቻ፣ አንድ ጠብታ ክትባት ብቻ ነው የሚያስፈልገው በሚል የተሰላ ሲሆን ይህ ግምት ለምሳሌ በእጥፍ ቢጨምር እጥፍ ካርጎ አውሮፕላን ያሻል ማለት ነው፡፡

የአየር ትራንስፖርት ማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አሌክሳንደር ዴ ጁኒያክ እንዲህ ተናግረዋል፣ ‹‹የኮቪድ 19 ክትባትን በጥንቃቄ ማጓጓዝ የዚህ ክፍለ ዘመን ትልቁ የካርጎ ኢንዱስትሪ ግብ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲሁ በዘፈቀደ የሚጓጓዝ አይደለም፤ ከፍተኛ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ ለዝግጅቱ ትክክለኛው ጊዜ ደግሞ አሁን ነው››

በርካታ አየር መንገዶች በወረርሽኙ ጊዜ የሰዎች ከቦታ ቦታ እንቅስቃሴ በመታቀቡ ወደ ካርጎ ሥራ ገብተው ቆይተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ይጠቀሳል፡፡

ነገር ግን ማንም እቃ የሚያጓጉዝ አየር መንገድ ክትባትን ማጓጓዝ ይችላል ማለት አይደለም፡፡

ክትባት ለማጓጓዝ ካርጎው ከ2 እስከ 8 ሴንትግሬድ የሙቀት መጠን ሊኖረው ይገባል፡፡

አንዳንድ ክትባቶች ደግሞ እጅግ ቀዝቃዛ (ከዜሮ በታች) የሆነ የሙቀት መጠንን ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ይህን ማሟላት ለብዙ አየር መንገዶች ፈተና ሊሆን ይችላል፡፡ ዝግጅት ከወዲሁ የተጀመረውም ለዚሁ ነው፡፡

ይህንን ክትባት የማጓጓዙን ፈተና ለመቀነስ አንዱ መንገድ አገራት በየራሳቸው ክትባቱን እንዲያመርቱት ማድረግ ቢሆንም ይህ ለብዙ የዓለም አገራት የሚቻል አይሆንም፡፡

በተለይ በርካታ የካርጎ በረራዎች ወደ ደቡብ ምሥራቅ ኢሲያ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በርካታ ሕዝብ ስለሚገኝና ክትባት የማምረት አቅም ያለው አገርም ባለመኖሩ ነው፡፡

ክትባቱን በቀላሉ ወደ አፍሪካ ለማጓጓዝም የሚቻል አይደለም ብሏል ማኅበሩ፡፡ ይህም በቂ የካርጎ አቅም ስለሌለ፣ አፍሪካ ሰፊ አህጉር በመሆኗና የድንበር ውስብስብነት መኖሩ ነው፡፡

የካርጎ ሥራው ልክ ወታደራዊ ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው፤ ከተጓጓዘ በኋላም ቢሆን የሚቀመጥበት ቦታ መድኃኒቱን ለማስቀመጥ የሚሆን መሆን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ለበርካታ የአፍሪካ አገሮች ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዓለም ደረጃ 140 ቤተ ሙከራዎች ክትባት ለመሥራት ተፍ ተፍ ማለት ጀምረው ነበር፡፡ አሁን 24 የሚሆኑት በሰዎች ላይ ሙከራ ጀምረዋል፡፡ ከነዚህ ሁሉ ትልቅ ተስፋ የተሰጠው የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲው የክትባት ሙከራ ነው፡፡.

ሩሲያ ክትባቱ በእጄ ገብቷል ብትልም ዓለም በአገሪቱ ላይ እምነት በማጣቱ ይመስላል እምብዛምም የራሺያ ክትባት አይወራም፡፡

የጤና ባለሙያዎች የሩሲያ ክትባት ሳይንሳዊ ሂደትን የተከተለ አይደለም፣ ብሔራዊ ኩራተን ከጤና አስበልጧል ሲሉ ይተቹታል፡፡