በአማራና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የተከሰተው ምንድን ነው?

የፀጥታ አባላት ምርጫውን ሲያስተባብሩ

ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ በተለይም በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት እንደነበር የአካባቢው የፀጥታ አካላት ለቢቢሲ ተናገሩ።

ቢቢሲ የሁለቱንም ክልል የፀጥታ ኃላፊዎች ያነጋገረ ሲሆን አንዳቸው በሌላኛቸው ክልል ወገን ግጭት መቀስቀሱን ገልፀዋል።

ቢቢሲ በአማራ ክልል ሥር የሚገኘው የጠገዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ሙሉጌታ ስለ ጉዳዩ ጠይቆ፣ እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ወረዳ ምንም ግጭት አለመኖሩን ገልጸው በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የጸገዴ ወረዳ ግን ከምርጫው ጋር ተያይዙ ግጭት መኖሩን እንደሰሙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የትግራይ ክልል ፀጥታ ከፍተኛ ኃላፊም በምዕራብ ትግራይ ጸገዴ አካባቢ በትግራይ መሬት ገብቶ የተኮሰ አካል እንደሌለ በመግለጽ "በአማራ ክልል ውስጥ ግን ተኩስ እንደነበረ ሰምተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ሙከራ "ህዝብን ለማደናገጥ የታሰበ" ቢሆንም ህዝቡ ግን በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ሰጥቷል ብለውናል ያነጋገርናቸው የጸጥታ ሃላፊዎች።

የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከቢቢሲ ኒውስ ደይ የሬድዮ ፕሮግራም ላይ በነበራቸው አጭር ቆይታ በትግራይ ደቡብ አካባቢ ምርጫውን የማደናቀፍ ሙከራዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

"አሁን ካንተ ጋር በምነጋገርበት ሰዓት በትግራይ ደቡብ አካባቢ ድንበር ላይ ግጭት ለማንሳት የሚሞክሩ ሰዎች አሉ። እኛም እነዚህ ትንኮሳዎችን ስንመክት ቆይተናል" ሲሉም ለጋዜጠኛው አስረድተዋል።

የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ "የትምክህት ሃይሎች" ሲል በገለጻቸው አካላት ከምርጫ ጣቢያ ራቅ ባለ አካባቢ ትንኮሳ እንደነበር በፌስቡኩ አሳውቋል።

"በቂ ሃይል ስላለ ትንኮሳው አልተሳካም። ሙከራው ለደቂቃዎች ብቻ እንደነበረም ለማወቅ ችለናል" ብሏል ኮሚሽኑ።

በሌላ በኩል የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክብረዓብ ቸርነት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው የጸገዴ ወረዳ ውስጥ ልዩ ስሙ ጨቋር ኩዶቢን በሚባል ቦታ ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ የትግራይ ልዩ ኃይል ነዋሪው ወጥቶ እንዲመርጥ እና ሚሊሻው ደግሞ "አማራ ሊወርህ እየመጣ ስለሆነ መንገድ ዝጋ" የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ይገልጻሉ።

ነገር ግን ሕዝቡ የመምረጥም ሆነ መንገድ የመዝጋት ፍላጎት አልነበረውም የሚሉት አቶ ክብረዓብ ሕዝቡ ምላሽ ባለመስጠቱ "ከትግራይ ልዩ ኃይል በኩል ተኩስ ተከፈተበት" ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም ሕዝቡ ራሱን በመከላከሉ ግጭት ተነስቶ እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም በነበረው የተኩስ ልውውጥ ጉዳት እንዳልደረሰ ገልጸዋል።

አሁን አካባቢው የተረጋጋ ቢሆንም ምርጫውን ተከትሎ ግን የተለየ ነገር ሊኖር እንደሚችልም ገልጸዋል።

ባለፉት ወራት በአካባቢው ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲካሄዱ እንደነበር የሚገልፁት አቶ ክብረአብ ይህንንም ለሚመለከታቸው አካላት ቢያመለክቱም እስካሁን መልስ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊትም የምርጫ ካርድ ለምን አላወጣችሁም በሚል ሳቢያ ከ500 በላይ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ወጣቶች በትግራይ ክልል መንግሥት መታሰራቸውን የማንነት ኮሚቴው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጸዋል።