"ሀረማያ ሀይቅ ቢመለስም መልሶ ከመድረቅ ነጻ አይደለም" -ባለሙያዎች

የሀረማያ ሀይቅ ላይ ሰዎች ሲዋኙ

የፎቶው ባለመብት, የምስራቅ ሐርጌ አካባቢ ጥበቃ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን

የምስሉ መግለጫ,

በዚህ የክረምት የዝናብ ወቅት የሀረማያ ሀይቅ ከነበረው የስፋት መጠን 61 በመቶ ተመልሶ በውሃ ተሸፍኗል

እስክንድር የሱፍ ዑመር ተወልዶ ያደገው በሀረማያ ሀይቅ አካባቢ ነው። ሀይቁን በቀደመ ሞገሱና ዝናው ያውቀዋል። በሃይቁ ላይ ጀልባ ቀዝፎ፣ አሳ አጥምዶ ያውቃል።

"እውነት ለመናገር የሀረማያ ሀይቅ በመድረቁ እናት እና አባት እንደሞተብን ይሰማን ነበር" የሚለው እስክንድር ሰሞኑን የሀይቁን ዳግምም መሙላት ተከትሎ በልጅነቱ በሀይቁ ላ ይዝናና እንደነበረው ለመዝናናት፣ ጀልባ እያሰራ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በዚህ የክረምት የዝናብ ወቅት የሀረማያ ሀይቅ ከነበረው የስፋት መጠን 61 በመቶ ተመልሶ በውሃ መሸፈኑን ባለሙያዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ይህ ደግሞ የእስክንድርንም ሆነ ሌሎች የአካባቢ ነዋሪዎች በደስታ አስፈንጥዟል።

የሀረማያን ሀይቅ በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ግን ሀይቁ ቢመለስም ተመልሶ ከመድረቅ ስጋት ነጻ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የዘንድሮው ክረምት፣ የዝናብ ስርጭት እንደ አገር ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት በሀረማያ ዩኒቨርስቲ ሀይድሮሊክና የውሃ ሃብት መሀንዲስ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ኢንጂነር ተሾመ ስዩም፣ በአካባቢው ዘንድሮ ከፍተኛ ዝናብ በመዝነቡ፣ ሀይቁ ውሃ ለመያዝ ችሏል ሲሉ ገልጠዋል።

ይኹን እንጂ ከደረቀበት ከሃያ ዓመት በፊት ጀምሮ በዚህ መልክ ውሃን ሲይዝ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ገልፀዋል።

የሀረማያ ሃይቅ ከሁለት ዓመት በፊት በዚህ መልኩ ውሃ ይዞ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

ነገር ግን ውሃ ይዞ መቆየት አልቻልም ያሉት ዶ/ር ተሾመ፣ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለመስኖ ከሀይቁ ብዙ ውሃ ስለሚጠቀሙ መሆኑን አብራርተዋል።

"በሀረር አካባቢ ብዙ የተቆፈሩ ጥልቅ የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶች አሉ፤ ስለዚህ ወደ ሀይቁ የገባው ውሃ እና ህዝቡ የሚገለገልበት መጠን ከፍተኛ ልዩነት ስላለው ውሃው ተመልሶ ይደርቃል" ሲሉ ዶ/ር ተሾመ ስዩም የተፈጠረውን ያስረዳሉ።

ለሀረማያ ሀይቅ መድረቅ አንዱ ምክንያት የውሃ የአስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት አለመኖር እንደሆነ ምሁሩ አክለዋል።

በሀረማያ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች የውሃ አጠቃቀም ላይ ችግር እንዳለ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ወደ ሀይቁ የሚገባው ውሃ እና ሕዝቡ የሚገለገልበት እንደማይመጣጠን ገልፀዋል።

"የሚገባው ውሃ ትንሽ ነው፤ ኀብረተሰቡ ለመስኖ እና ለመጠጥ ውሃ የሚጠቀምበት ብዙ ስለሆነ ውሃ ሊጠራቀም አልቻለም።"ይላሉ

በአሁኑ ጊዜ ሀረማያ ሀይቅ ይዞ የሚገኘው ውሃ ትልቅ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው፣ ውሃው ሀይቁ ውስጥ እንዲቆይ የሚፈለግ ከሆነ "በውሃ አጠቃቀም ላይ ሕግ መኖር አለበት" ሲሉ ይመክራሉ።

" በዓመት ምን ያህል ውሃ ወደ ሀይቁ ገባ? ኀብረተሰቡ ደግሞ ምን ያህሉን ይጠቀማል? የሚለውን ለመረዳት ሚዛናዊ የውሃ አጠቃቀምን መኖሩን መፈተሽ ያስፈልጋል።"

ይኹን አንጂ የአካባቢው አርሶ አደሮች ሀይቁ የያዘውን ውሃ በሙሉ ለመስኖ የሚጠቀሙ ከሆነ፣ የሀይቁ መቆየት ጥያቄ ውስጥ እንደሚወድቅ ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

ይህንን ለመከታተል ደግሞ ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ መኖር እንዳለበት ጨምረው ገልፀዋል።

ከዚህም በፊት በውሃ አጠቃቀም ደንብ ላይ ውይይት መደረጉን የሚጠቅሱት ዶ/ር ኢንጂነር ተሾመ፣ በምክክሩ የተሄደበት መንገድ ተገቢ እንዳልነበር ያስታውሳሉ።

አንድ ሕግ ሲረቀቅ ከህዝቡ ጋር መወያየት እንደሚያስፈልግ የሚገልፁት ምሁሩ፣ ባለሙያዎችን ብቻ ማወያያት ውጤታማ እንደማያደርግ ይገልፃሉ።

በተጨማሪም የውሃ አጠቃቀም ሕግ ከወጣ በኋላም በሰነድነት ብቻ እንዲቀመጥ ሳይሆን፣ ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚያስፈልግም ያብራራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Sentinel Hub and European Space Agency (ESA)

ሀረማያ በውሃ እንደተሞላ አንዲቆይ ምን ይደረግ?

የሀረማያ አካባቢ አርሶ አደሮች በሚሰሩት የመስኖ ስራ ብዙ የውሃ ብክነት እንዳለ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ስለዚህ አርሶ አደሮቹ ውሃ ቆጣቢ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ኀብረተሰቡን ማስተማር እና ግንዛቤ ማስጨበጥ የመፍትሄው አካል መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ።

"ይህ ሀይቅ ባለቤት የሌለው ከሆነ ተመልሶ ይደርቃል፤ ይህ መታወቅ አለበት" ይላሉ ዶ/ር ኢንጂነር ተሾመ።

ከዚህም ሌላ የሀረማያ ሀይቅ ድንበር የሌለው እንደመሆኑ መጠን ሀይቁ እንዲቆይ በማካለል ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀምበት ማድረግ ያሻል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሀረማያ ሀይቅ በሕይወት እንዲቆይ ለማድረግ የተፋሰስ ልማትን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ እየታጠበ ወደ ሀይቁ የሚገባውን አፈርን ለመቆጣጠርና ውሃ በስርዓቱ ወደ ሀይቁ እንዲፈስ ለማድረግ አስራ አምስት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት መሰራት እንደሚያስፍልግ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ይኹን አንጂ እስከዛሬ የተሰራው የተፋሰስ ልማት በቂ እንዳልሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።

ችግኞች መትከልና መንከባከብን አከታትሎ መስራትን እንደሚጠይቅ የሚናገሩት እኚህ ምሁር "ሀይቁ አዋሳኝ አካባቢዎች አፈር ታጥቦ እንዳይገባ ሳር መትከል ላይ መስራት በጣም ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።

የምስራቅ ሐርጌ አካባቢ ጥበቃ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን፣ የአካባቢ ጥበቃና ክትትል ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ አብዱላዚዝ አህመድ፣ በበኩላቸው ወደ ሀይቁ የሚጣለው ቆሻሻ ችግር እንደሆነ በማንሳት የአካባቢው ኀብረተሰብ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ተማጽነዋል።