ሳይንቲስቶች የዓለም የዱር እንስሳት ቁጥር "በሰው ልጅ ጥፋት የተነሳ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ" መሆኑን አስጠነቀቁ

በታይላንድ በደን ምንጣሮ ስራ ላይ የተሰማራ ዝሆን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የዱር እንስሳት በደን ምንጣሮና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ እየጠፉ ነው

የዓለማችን የዱር እንስሳት ቁጥር ከሃምሳ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሁለት ሶስተኛ ቁጥራቸው መቀነሱን የዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ቡድን (WWF) ያወጣው የጥናት ሪፖርት ገለፀ።

ጥናቱ ይፋ እንዳደረገው የዱር እንስሳቱ ቁጥር "በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ" ሲሆን ምንም አይነት መረጋጋትም ሆነ መቆም እንደማይታይበትም ተገልጿል።

ይህ ጥናት ተፈጥሮ በሰው ልጆች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየወደመች መሆኑን በማንሳትም አስጠንቅቋል።

የዱር እንስሳት ደኖች ሲቃጠሉ፣ የባህር ዓሳዎችን ከተገቢው በላይ ስንጠቀም እንዲሁም መኖሪያቸውን ስናወድም "በአስደንጋጭ ሁኔታ ቁጥራቸው እየቀነሰ ነው" ያሉት የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ታንያ ስቴሌ ናቸው።

"አለማችንን እያናጋናት ነው፤ ቤታችን ብለን የምንጠራትን፤ ጤናችንን፣ ደህንነታችንን እንዲሁም ምድር ላይ ለመቆየት የሚረዳንን ነገር። አሁን ተፈጥሮ መልዕክቷን የላከችልን ሲሆን፣ ጊዜ ደግሞ ከእኛ ጋር አይደለም" ብለዋል።

የድርጅቱ ጥናት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስቶች በዓለም ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የዱር እንስሳት ዝርያዎችን በቅርበረት ከተከታተሉ በኋላ የቀረበ ነው።

እኤአ ከ1970 ወዲህ ጀምሮ ከ 20 ሺህ በላይ አጥቢዎች፣ አእዋፋት፣ የአሳ ዝርያዎች፣ ተሳቢ እንስሳት፣ እንዲሁም 'አምፊቢያንሶችን' ተመልክቶ በአማካይ በ68 በመቶ ቁጥራቸው መቀነሱን አስቀምጧል።

የእንስሳቱ ቁጥር መቀነስ በሰው ልጅ በሚያደርሰው ውድመት የተነሳ መከሰቱን ግልጽ ማስረጃ ነው የሚሉት በለንደን ዞሎጂካል ሶሳይቲ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አንድሪው ቴሪ ናቸው።

"ምንም የሚለወጥ ነገር ከሌለ፣ ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱ አይቀርም። ይህ ደግሞ የዱር እንስሳቱ እንዲጠፉ እንደሚያደርግ እና የምንኖርበት ስነ ምህዳር አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ጥናቱ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን የሰው ልጅና ተፈጥሮ ምን ያህል የተጋመዱ መሆናቸውን ለማስታወስ በቂ ነው ሲል ያትታል።

ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቀስቀስ ምክንያት እንደሆኑ ከሚታመኑ ነገሮች መካከል አንዱ የዱር እንስሳት ንግድ ሲሆን ይህ ደግሞ ለቁጥራቸው መቀነስም ሌላኛው አስረጅ ነው ተብሏል።