ኮሮናቫይረስ፡ በካናዳ አንዲት ጨቅላ ሕጻን ጭምብል ባለማጥለቋ በረራ ተሰረዘ

መንገደኞች በአየር ማረፊያው ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Submitted photo

ነገሩ አስገራሚ ነው፡፡ በካናዳ አንዲት ጨቅላ ሕጻን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረጓ ብቻ ፖሊስ ተጠርቷል፣ በረራውም ተሰርዟል፡፡

ሕጻኗ ከተወለደች ገና 19 ወሯ ነው፡፡

ዌስት ጄት ደግሞ ሁሉም ተሳፋሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማጥለቅ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ጨቅላዋ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሲደረግላት እሪታዋን ታቀልጠዋለች፡፡

ብትባል ብትሰራ እምቢኝ ትላለች፡፡ እናትና አባት ያልሞከሩት ነገር የለም፡፡ ሕጻኗ ሞቼ እገኛለሁ አለች፡፡ የአየር መንገዱ አስተናጋጆችና ቤተሰብ አንድ ሁለት ሲባባሉ ነገሩ ተካሮ በረራ እስከመሰረዝ ደርሷል፡፡

አየር መንገዱ ግን ታሪኩ ሌላ ነው ይላል፡፡

የ19 ወር ጨቅላዋ አይደለችም ችግር የፈጠረችብኝ ብሏል ዌስትጄት፡፡ እንዲያውም በሷ ደረጃ ያሉ ሕጻናት ጭምብል እንዲያጠልቁም አይገደዱም ብሏል፡፡

ታዲያ ለምን በረራውን ሰረዛችሁ ሲባል ሌላ የጨቅላዋ ታላቅ እህት አለች፤ 3 ዓመቷ ነው፡፡ እሷ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጥልቂ ስትባል እምቢ በማለቷ ነው በረራውን እንድንሰርዝ የተገደድነው ብሏል፣ ዌስትጄት፡፡

የሕጻናቱ እናትና አባት፣ እንዲሁም ተሳፋሪዎች ግን" ዌስትጄት ቀጣፊ ነው፣ ዋሽቷል፤ የ3 ዓመቷ ልጅ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጋ ነበር ሲሉ "ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ግርግር በሞባይል የተቀረጸ ቪዲዮም የ3 ዓመቷ ልጅ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጋ ነው የምትታየው፡፡

ፖሊስም በበኩሉ እኔ ስደርስ ታላቅየው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጋ ነበር ብሏል፡፡

ይህ የሆነው ማክሰኞ ነው፤ ከትናንት በስቲያ፡፡

በረራው ከካልጋሪ ተነስቶ ቶሮንቶ የሚደርስ ነበር፡፡

በረራ 652 ግን ከመነሻው ሳይሳካ ቀርቶ ሁሉም ተሳፋሪዎች ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ተደርገዋል፡፡

የልጆቹ አባት አቶ ኮድሀሪ እንዲህ ዓይነት ጉድ በፍጹም ያጋጥመኛል ብዬ በሕልሜም በእውኔም አስቤም ጠብቄም አላውቅም ብሏል ለቢቢሲ፡፡

‹‹እኔና ባለቤቴ ከሁለቱ ሴት ልጆቻችን ጋር ነበርን፤ አውሮፕላኑ ሊነሳ ሲል የሦስት ዓመቷ ልጄ ቁርስ ቢጤ እየበላች ነበር፡፡ የበረራ አስተናጋጇ መጥታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንድታጠልቅ ነገረቻት፡፡ እኔና እናቷ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገናል፤ የ3 ዓመቷ ልጃችን ደግሞ እየበላች ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡

‹‹የበረራ አስተናጋጇ ዌስትጄት በአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጉዳይ ጥብቅ ፖሊሲ እንደሚከተልና ልጃቸው ቁርሱ መብላቷን ትታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ካላጠለቀች በረራው እንደማይደረግ ነገረችን›› ይላል አባት፡፡

‹‹ልጆች ደግሞ በአንድ ጊዜ መታዘዝ እሺ ስለማይሉ ማባበል ጀመርኩ፡፡ የ3 ዓመቷ ልጄ ትንሽ ካስቸገረችን በኋላ እሺ ብላ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዋን አጠለቀች፡፡››

‹‹ታናሽየው ግን እምቢኝ አለች፤ እንዲያውም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛውን ስናደርግላት ወደላይ አላት›› ይላል አባት፡፡

‹‹ዌስትጄት ትእግስት አልፈጠረባቸውም፡፡ ትንሽዋ ልጄ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ስላላጠለቀች አውሮፕላኑ እንደማይበር ነገሩን፡፡››

እንዲያውም ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ እንደታዘዙና አንወርድም ካሉ ግን እንደሚታሰሩ እንደተነገራቸው ለቢቢሲ አስታውቋል፡፡

በዚህ ጊዜ ከአውሮፕላኑ ለመውረድ ተስማማን ብሏል አባት ለቢቢሲ፡፡

አባት በረራው ከተሰረዘ በኋላ ተረዳሁ እንደሚለው ከሆነ ‹‹በካናዳ ትራንስፖርት ፖሊሲ መሰረት የ19 ወሯ ጨቅላ ልጃቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማጥለቅ አትገደድም ነበር፡፡››

ዌስትጄት ባወጣው መግለጫ ግን በረራው የተሰረዘው የ19 ወሯ ጨቅላ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ስላላጠለቀች ሳይሆን የሷ ታላቅ የ3 ዓመቷ ህጻን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ነው ብሏል፡፡