አሜሪካ የ1ሺህ ቻይናዊያን ተማሪዎችን ቪዛ ሰረዘች

የተማሪ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ለደኅንነቴ ያሰጉኛል በሚል የ1ሺህ ቻይናዊያን እና ተመራማሪዎችን ቪዛ መሰረዟን አስታወቀች፡፡

ይህ እርምጃ ባለፈው ግንቦት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹ቻይናዊያን ተማሪዎች መረጃ ይሰርቃሉ፤ ፈጠራ መብትን ይመነትፋሉ›› ብለው ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ የተወሰደ የመጀመርያ ውሳኔ ነው፡፡

ቻይና በጉዳዩ ላይ ለጊዜው ምንም ያለችው ነገር የለም፡፡

በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች በ2018 እና 19 ብቻ 370ሺህ ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበኩሏ ‹‹ቪዛ የከለከልናቸው 2ኛ ዲግሪና የምርምር ሥራ ላይ ሊሰማሩ የነበሩትንና ስጋት የሆኑት ብቻ ነው››ብላለች፡፡

ይህ ቁጥር ከጠቅላላ የቻይና ተማሪዎች ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡

‹‹ቻይናዊያን ተማሪዎች አገራችን ገብተው እንዲማሩ አንከለክልም፡፡ ዓለማቸው ለኮሚኒስቱ ፓርቲ መረጃ ማቀበል እስካልሆነ ድረስ›› ብላለች ቃል አቀባይዋ፡፡

በግንቦት ወር በአሜሪካ የወጣው መመሪያ የቻይና መንግሥት ቻይናዊ ተማሪዎችን በመጠቀም ለብሔራዊ ደኅንነት አደገኛ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከአሜሪካ ይጠልፋል፣ የፈጠራ መብቶችን ይመነትፋል፣ ወሬም ያቀብላል ሲል ያውጃል፡፡

አንዳንድ በአሜሪካ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ቻይናዊያን በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በካምፓሶች ውስጥ በጥርጣሬ እንደሚታዩና የጥላቻ ንግግሮችን እንደሚያስተናግዱ በመግለጽ ሁኔታዎች እንዲለወጡ ጠይቀዋል፡፡