'ሰለብሬሽን' በሚል ዜማቸው የሚታወቁት ኩል ኤንድ ዘ ጋንግ ባንድ መስራች አረፈ

ሮናልድ ቤል ከወንድሙ ሮበርት ጋር
የምስሉ መግለጫ,

ሮናልድ ቤል ከወንድሙ ሮበርት ጋር

በበርካታ ምርቃቶች ላይ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የሚሰማ ዘፈን አለ 'ሰለብሬሽን" የሚል።

ድንበር፣ ቋንቋን ተሻግሮ የሰው ልጅ የሚያመሳስለው ነገር በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ የሚያበስር ዘፈን።

ከእነዚህም አንዱ የደስታ መግለጫ ነው።

ሰለብሬሽንም ዘመንን ተሻግሮ አሁንም ይሰማል፤ ለሰው ልጅ ደስታም አስፈላጊ እንደሆነ ያዜማሉ።

ይህንን ዜማ የተጫወቱት ደግሞ የሶውልና ፈንክ ተብሎ የሚታወቀውን የሙዚቃ አይነትን በማጣመር የሚጫወቱት የአሜሪካውያኖቹ ኩል ኤንድ ዘ ጋንግ የተባለው ባንድ ነው።

ከሰሞኑም አንደኛው መስራች ሮናልድ ቤል በ68 ዓመቱ ህይወቱ አልፏል።

ሮናልድ ባንዱን የመሰረተው ከወንድሙ ሮበርት (ኩል) ቤል ጋር ነው።

ባንዱ በ70ዎቹና 80ዎቹ የዝና ጣራ ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን በተለይም ሰለብሬሽን፣ ሌዲስ ናይትና ጀንግል ቡጊ በሚሉ ዜማዎቻቸውም ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፈዋል።

ሙዚቃዎቻቸው 'ሳተርደይ ናይት ፊቨር' የሚለውን ፊልም ጨምሮ ለተለያዩ ፊልሞች ማጀቢያነትም ውሏል። በዚህም ፊልም ማጀቢያነት በጎርጎሳውያኑ 1978 የግራሚ ሽልማትን እንዲሁም የፐልፕ ፊክሽን ሽልማቶችን አሸንፈዋል።

ሮናልድ ቨርጂን አይላንድስ በሚገኘው ቤቱም ባለቤቱ ከጎኑ ባለችበት ህይወቱ እንዳለፈም ተጠቅሷል።

በምን ምክንያት ህይወቱ እንዳለፈ ግን የተባለ ነገር የለም።

ራሱን ሳክስፎን ያስተማረው ሙዚቀኛው ሮናልድ ባንዱን ከወንድሙ ሮበርት፣ ዴኒስ ቶማስ፣ ሮበርት ማይክንስ፣ ቻርልስ ስሚዝ፣ ጆርጅ ብራውንና ሪኪ ዌስት ጋር በመሆን ባንዱን የመሰረተው በጎርጎሳውያኑ 1964 ነበር።

ባንዱም ሶውል፣ ጃዝ፣ ፈንክ፣ ዲስኮ፣ አር ኤንድ ቢ፣ ፖፕና ዲስኮን ስልቶችን በማጣመር ይታወቃል።

"ከሁሉም ዘፈናችን ውስጥ የምወደው ሰለብሬሽንን ነው፤ እንዲህ ዝናው የናኘ እንደሚሆን አላወቅኩም ነበር " በማለት ሮናልድ ቤል ለሮይተርስ በ2008 ተናግሮ ነበር።

"ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላም በርካታ ሰዎች ሲዘፍኑት፣ ዘፈኑን እየሰሙ ሲፈነድቁ ሳይ በጣም ደስታ ይሰማኛል" ብሎ ነበር።

በዓለም ላይ በኢንተርቴይንመንት ኢንዱስትሪው ላበረከቱት አስተዋፅኦም በሆሊውድ ዋክ ኦፍ ፌም ኮከብ ተቀምጦላቸዋል።