የአንጀሊና ጆሊን አንጀት የበሉት ሁለት ሕጻናት

አንጀሊና ጆሊ ከየመን ህፃናት ጋር

የፎቶው ባለመብት, BBC/Adeela Moosa

ዝነኛዋ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ ሰሞኑን ያልተጠበቀ ነገር አድርጋለች፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡-

ሁለት ለንደን የሚገኙ ትንንሽ ልጆች የመን ያሉ እኩዮቻቸው ተርበው፣ ተጠምተው፣ ታርዘው በቴሌቪዥን ይመለከታሉ፡፡

ባዩት ነገር ልባቸው ይነካል፡፡ ገና እኮ 6 ዓመታቸው ነው፡፡

ከዚያ እኩዮቻችንን መርዳት አለብን ብለው ተነሱ፡፡ መንገድ ላይ የሎሚ ጭማቂ መሸጥም ጀመሩ፡፡

ከዚያ እየሸጡ እየሸጡ ሳንቲም እያጠራቀሙ ለየመን ልጆች ይልካሉ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን የሆነ ደብዳቤ ደረሳቸው፤ አንጀሊና ጁሊ ከምትባል ሴትዮ፡፡

ደብዳቤው እንዲህ ይላል፡፡

‹‹እኩዮቻችሁን ለመርዳት ሎሚ ጭማቂ መሸጥ ስለጀመራችሁ አመሰግናለሁ፡፡ የሎሚ ጭማቂ ልገዛችሁ ባለመቻሌ አዝናለሁ፡፡ ነገር ግን እኔም ማገዝ እፈልጋለሁ፡፡››

በምሥራቅ ለንደን የሚገኙት ሁለቱ አዳጊዎች አያን ሞሳ እና ሚኪል ኢሻቅ ይባላሉ፡፡

አንጀሊና ስለ ሁለቱ ልጆች በጎ ድርጊት የሰማችው የቢቢሲን ድረገጽ በምታነብበት ጊዜ ነበር፡፡

በልጆቹ ድርጊት ክፉኛ ልቧ በመነካቱ ሎንዶን ወደሚገኘው ወኪሏ ደውላ አንድ ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ አለች፡፡

የልጆቹ ወላጆች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በጎ ሥራ ላይ የነበሩት ልጆቻቸው አንጀሊና ማን እንደሆነች አያውቁም ነበር፡፡ ደብዳቤው ሲነበብላቸውም ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡

በኋላ ላይ አንጀሊና ማለት ቱም ሬይደር (Tomb Raider) ፊልም ላይ ያለችው ተዋናይት መሆኗን ሲረዱ ደነገጡ፡፡

ልጆቹ የአንጀሊናን ደብዳቤና ልዩ ስጦታ ከደረሳቸው በኋላ ራሳቸውን ቪዲዮ ቀርጸው በምላሹ እንዲህ ብለዋታል፡፡

ውድ አንጀሊና፡- ‹‹ስለእርዳታሽ እናመሰግናለን፡፡ ሎንደን ከመጣሽ ፍሬሽ የሎሚ ጭማቂ እንሸጥልሻለን››

ሁለቱ አዳጊዎች የብርቱካን ጭማቂ በመሸጥ እኩዮቻቸውን ለመርዳት ባሳዩት ልብ የሚነካ ተግባር እስከ አሁን ወደ 70ሺ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አሰባስበዋል፡፡

አንጀሊና ሕጻናቱ ከሰበሰቡት ገንዘብ መካከል ምን ያህሉን እንዳዋጣች የተገለፀ ነገር የለም።