ቬነስ ላይ ሕይወት ይኖር ይሆን?

ቬኒስ

የፎቶው ባለመብት, JAXA/ISAS/Akatsuki Project Team

ከሚሊዮን አንዴ እንደሚሉት ነው ይህ አጋጣሚ። ቬነስ የተሰኘችው ፕላኔት ላይ ሕይወት ይኖር ይሆን?

የጠፈር ሳይንስ ልሂቃን ቬነስ ላይ ጋዝ አግኝተዋል። ይህ ደግሞ ፕላኔቷ ሕይወት ያለው ነገር ይዛ ይሆን? ወደ ሚል ጥያቄ እንዲያመሩ አድርጓቸዋል።

የተገኘው ጋዝ ፎስፊን ነው። ከአንድ ፎስፈረስ አተምና ከሦስት የሃይድሮጅን አተሞች የተሠራ።

ጋዙ የተገኘው የቬነስ ደመና ላይ እንደሆነም ተነግሯል።

ምድር ላይ ፎስፊን ሕይወት ካላቸው ነገሮች ጋር ግንኙነት አለው። በተለይ ደግሞ ፔንግዊንን በመሳሰሉ ኦክስጅን በሚያጥራቸው ሥፍራዎች በሚኖሩ እንስሳት ጋር የቀረበ ትስስር አለው።

እርግጥ ነው ፎስፊን በፋብሪካ ሊመረት ይችላል። ነገር ግን ቬነስ ላይ ፋብሪካ የለ፣ ፔንግዊንም የለም።

እና ጋዝ ቬነስ ላይ ምን ይሠራል?

የካርዲፍ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ጄን ግሪቭስ ጥያቄም ይሄው ነው።

ፕሮፌሰሩና የሥራ ባልደረቦቻቸው ፎስፊስን ቬነስ ላይ ምን ይሠራል የሚለውን ጥያቄ የሚያብራራ ጽሑፍ አሳትመዋል። ጽሑፋቸው ያደረጉትን ምርምርና ጋዙ ምናልባት ባዮሎጂካል ያልሆነ ሊሆን እንደሚችል እንደሚጠረጥሩ ያስረዳል።

ነገር ግን ተመራማሪዎቹ ምሉዕ የሆነ ምላሽ ስላላገኙ አሁንም መገረማቸው አልቀረም።

ምንም እንኳ የሰው ልጅ እስከዛሬ ስለ ቬነስ መድረስ የቻለውን ያህል ቢያውቅም ፎስፊን ባዮሎጂካል ባልሆነ መንገድ ፕላኔቷ ላይ ስለመፈጠሩ የሚያውቀው ነገር የለም።

ይህ ማለት ቬነስ ላይ ሕይወት ያለው ነገር ሊኖር ይችላል የሚለው ሐሳብ ውሃ እንዲያነሳ ሆነ ማለት ነው።

"ሕይወቴን መሉ ከምድር ውጪ ሌላ ቦታ ሕይወት ይኖር ይሆን ወይ የሚለውን ሳጠና ነው የኖርኩት። አሁን ይህ እውን ሊሆን እንደሚችል በማወቄ በጣም ተደንቄያለሁ" ይላሉ ፕሮፌሰር ግሪቭስ።

"ሌሎች ሰዎች እኛ የተሳሳትነው ነገር ካለ ቢነግሩን መልካም ነው። የእኛ ጥናት ለሁሉም ክፍት ነው። ሳይንስ እንደዚህ ነው የሚሠራው።"

የፕሮፌሰር ግሪቭስ ቡድን ቬነስ ላይ ፎስፊን እንዳለ ማወቅ የቻለው ሀዋይ ውስጥ የተተከለውን የጄምስ ክለርክ ማክስዌል ቴሌስኮፕን በመጠቀም ነው።

ሌላኛው ጥቅም ላይ የዋለው መሣሪያ ቺሊ የሚገኘው አታካማ ላርጅ ሚሊሜትር ነው።

ጋዙ የታየው ከፕላኔቷ ምድር ወለል ከ50-60 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ደመና ላይ ነው።

ቬነስ እንዴት ያለች ነች?

ከምድር ውጪ ሕይወት ይኖር ይሆን ወይ የሚለው ሲታሰብ ቬነስ ቀድማ የምትመጣ ፕላኔት አይደለችም።

ከምድር ጋር ስትነጻጸር ቬነስ ገሃነም ናት። 96 በመቶ ከባቢ አየሯ ከካርበን ዳዮክሳይድ የተሠራ ነው።

ሙቀቷ ደግሞ እሳተ ገሞራ ነው። ልክ እንደ ፒዛ መጋገሪያ እሣት የተላበሰች ናት ቬነስ እስከ 400 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ትደርሳለች።

ወደ ቬነስ የተጓዙ ሳተላይቶች ልክ ፕላኔቷ ላይ ካረፉ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወድመዋል።

ቬነስ ላይ ሕይወት ከተገኘ ሊገኝ የሚችለው ደመና ላይ እንጂ ምድር ላይ የሚታሰብ አይደለም።

ለዚህም ነው ጋዙ 50 ኪሎ ሜትር ርቆ ደመና ላይ የተገኘው።

ሕይወትላይኖርይችላል?

የቬነስ ደመናዎች ወፍራም ናቸው። ከ75-95 በመቶ ከሰልፈሪክ አሲድ የተሰሩ ናቸው።

ምድር ላይ መሰል ደመና ውስጥ ሕይወት ያለው ነገር መኖር ይከብደዋል።

ተመራማሪዎች እዚህ የቬነስ ደመና ላይ ሕይወት ያለው ነገር ሊኖር የሚችለው ምናልባት የሰው ልጅ ባላወቀው የኬሚስትሪ ቀመር መሠረት ሊሆን ይችላል ይላል።

ከዚህ ውጪ ግን በሰልፈሪክ አሲድ በተሞላ ደመና ውስጥ ሕይወት ይኖራል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው ባይ ናቸው ሙያተኞቹ።

አጥኚዎች አሁንም ምርምራቸውን ቀጥለዋል። እርግጥ ነው ተመራማሪዎቹ ቬነስ ላይ ሕይወት አግኝተናል አላሉም። ነገር ግን ምርምራቸውን ገፍተውበታል።

ምላሽእንዴትማግኘትይቻላል?

ወደ ቬነስ ከባቢ አየር መንኮራኩር በመላክ።

የዩናይትድ ስቴትስ ጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ በ2030ዎቹ ወደ ሥፍራው ሊሄድ የሚችል መንኮራኩር ዲዛይን እንዲሠሩ ሳይንቲስቶችን ጠይቋል።

እኒህ መንኮራኩሮች በጣም ብቁና በጣም ውድ ናቸው።

ይህ የጠፈር አውሮፕላን ወደ ቬነስ ደመናዎች ተልኮ መረጃ መሰብሰብ ተልዕኮው ይሆናል ማለት ነው።