እባብ ፡ በሕይወት ያለ እባብን እንደ ጭምብል ለብሶ አውቶቡስ የተሳፈረው ግለሰብ

ግለሰቡ እባቡን አንገቱ ላይ ጠምትሞ አውቶብስ ውስጥ ተቀምጦ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ,

ግለሰቡ እባቡን አንገቱ ላይ ጠምትሞ አውቶብስ ውስጥ ተቀምጦ

ሕይወት ያለው እባብን እንደ ጭምብል አፉን አስኪሸፍን ድረስ በአንገደቱ ዙሪያ ጠምጥሞ አውቶቡስ የተሳፈረው ግለሰብ አግራሞት ፈጠረ።

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከስዊንተን ወደ ማንችስተር ከተማ በሚሄደው አውቶብስ ላይ የተሳፈረው ግለሰብ አንገቱ ላይ የጠመጠመው እባብ ነው ብለው አላሰቡም ነበር።

ሰውየው የአንገት ሹራብ ያደረገ ነበር የመሰላቸው ብዙዎቹ ተሳፋሪዎች። አንድ ተሳፋሪ ለቢቢሲ እንደገለጸችው እንዲሁ ስካርፍ ነበር የመሰለኝ ሲንቀሳቀስ ነው የደነገጥኩት ብላለች።

በማንችስተር የትራንስፖርት ስምሪት ተቆጣጣሪዎች እውነተኛ እባብ በዚህ በኮቪድ-19 ዘመን እንደ አፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አይቆጠርም ሲሉ ድርጊቱ ተቀባይነት እንደሌለው አረጋግጠዋል።

አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገች የዓይን እማኝ ነገሩ በጣም እንደገረማትና በጣም እንዳሳቃት ተናግራለች።

ጨምራም ግለሰቡ አንገቱ ላይ የጠመጠመው እባብ አብረውት ይጓዙ የነበሩት መንገደኞችን ይህን ያህል ያሰበረ አልነበረም ስትል መስክራለች።

በዩናይትድ ኪንግደም በሕዝብ መጓጓዣዎች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማጥለቅ ከ11 ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት ካልሆነ በስተቀር ግዴታ ነው። ነገር ግን በጤና ችግር ላይ ያሉ ሰዎች ወይም የተለየ ምክንያት ያላቸው ሰዎች ጭምብል እንዲያጠልቁ አይገደዱም።

የግሬተር ማንችስት ቃል አቀባይ በጉዳዩ ዙርያ ተጠይቆ "ጭምብል ለሰርጀሪ አይደለም የተፈለገው፤ ከምንም ይሰራ ምንም ይሁን አፍና አፍንጫን እስከሸፈነ ድረስ ስካርፍም ይሁን እባብ ምን ለውጥ ላይኖረው ይችላል" ብሏል።

ጨምሮም "…ነገር ግን አፍና አፍንጫን መሸፈን በምን በሚለው ዙርያ ሁሉንም የሚያስማማ ነገር ባይኖርም ነፍስ ባለው እባብ አፍና አፍንጫን መሸፈን ግን የሚጠበቅ አልነበረም" ሲል የግለሰቡ ድርጊት ያልተጠበቀ መሆኑን ተናግሯል።