ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፡ ኢሰመኮ አሳሳቢ መረጃዎች ከክልሉ እየደረሱት መሆኑን ገለጸ

የኢትዮጵያ ካርታ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ላይ አመለከተ።

ኮሚሽኑ እንዳለው እነዚህ መረጃዎች እየደረሱት ያለው በክልሉ ውስጥ ከሚገኘው መተከል ዞን፣ ከቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ እንዲሁም ከወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ በተጠቀሱት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሉ አንዳንድ ቦታዎች የሚያጋጥሙ ክስተቶችና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በእጅጉ እንዳሳሰበው በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

በመግለጫው ላይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጳጉሜ 1/2012 ዓ.ም እንዲሁም ከመስከረም 4 አስከ መስከረም 10/2013 ዓ.ም መካከል ባሉት ቀናት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግሥት ለማረጋጥ መቻሉን አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ ቢያንስ በሁለት ዙር በተፈጸሙ ጥቃቶች ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸውን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን በስፍራው ከሚገኝ አንድ መንግሥታዊ ምንጭ መረዳት እንደቻለ ኮሚሽኑ ገልጿል።

ስለሆነም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች፣ ግድያዎችና መፈናቀሎችን ሙሉ በሙሉ እንደሚያወግዝ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች ሰላምን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያበረታታም አስታውቋል።

እንዲሁም አገሪቱ በተቀበለቻቸው ሕጎችና ሰነዶች መሰረት የሰዎች በሕይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ የጠየቀ ሲሆን፣ በክልሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ገለልተኛ፣ ፈጣን ምርመራዎችን በማካሄድ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ አሳስቧል።

በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት አካላት ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቦ፤ በተለይም የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት ለማስከበር የሚመለከታቸው የክልሉ የመንግሥት አካላት እንዲሰሩ አሳስቧል።

መግለጫው አክሎ እንዳለው የክልሉ መንግሥት ከተፈናቃዮቹ መካከል 300 ያህል የሚሆኑት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንና የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በጋራ አካባቢውን ለማረጋጋት እየሰሩ መሆናቸውን መገልጹን ጠቅሷል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተለያዩ ጊዜያት ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ጥቃቶችና እገታዎች ሲፈጸሙ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከቀናት በፊት በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸው በስፋት እተገለጸ ነው።