እንግሊዛዊው ዶክተር ባለቤቱ አፍሪካዊ ስለሆነች ደም መለገስ አትችልም መባሉን ተቸ

ዶክተር ፍራንሲስ ጊታሄ

የፎቶው ባለመብት, Francis Gĩthae Murĩithi

በእንግሊዝ ተቀማጭነቱን ያደረገ ዶክተር ሚስቱ ኬንያዊ በመሆኗ ደም መለገስ አለመቻሉ "የማይረባና ትርጉም የለሽ" ህግ ነው ሲል ተቸ።

ዶክተሩ ፍራንሲስ ጊታሄ ሙሪቲ ይባላል ነዋሪነቱ በእንግሊዝ ይሁን እንጂ እሱም በትውልድ ኬንያዊ ነው።

እንግሊዝ ኤችአይቪ ወይም ኤድስ በተሰራጨባቸው አፍሪካ አገራት በቅርብ የመጡ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ደም መለገስ አይችሉም የሚል ህግን አፅድቃለች።

የእንግሊዝ የብሔራዊ ጤና ስርአትም በርካታ አፍሪካ አገራት ኤችአይቪ ኤድስ ስለተዛመተባቸው፣ ከነዚህ አገራት የመጡ ሰዎች ጋር በቅርብ ግንኙነት ከኖረዎትም ደም መለገስ አይችሉም ይላል።

ዶክተሩ የጥቁር ደም ለጋሾች ቁጥርን ለመጨመር ስርአቱ ሊቀየር ይገባልም በሚልም እየተከራከረ ነው።

ኤንኤችኤስ በበኩል ደምና የሰውነት አካላትን ልገሳን በተመለከተ ያለውንም ህግ እንደገና አጤነዋለሁ ብሏል።

የማህፀን ዶክተሩ ዶክተር ፍራንሲስ ከባለቤቱ ጋር ለሳበት አመታት የቆዩ ሲሆን፤ ከሌላ ሰውም ጋር ግንኙነት እንደሌላቸውና ትዳራቸው የፀና እንደሆነም ተናግሯል።

ዶክተሩ ከስራው ጋርም በተገናኘ በተደጋጋሚ የኤችአይቪ ምርመራ የሚያደርግ ሲሆን ውጤቱም ነፃ መሆኑን ያሳያል።

ሆኖም እሱ ደም እንዲለግስ ሚስቱ የኤችአይ ቪ ምርመራ እንድታደርግ ወይም ከወሲብ ለሶስት ወራት ያህል መቆጠብ አለባችሁ ተብለዋል።

ባለቤቱ ነፍሰጡር እያለች ምርመራ አድርጋ ነፃ መሆኗን ለኤንኤችኤስ ቢያሳውቅም ምንም ትርጉም የለውም ተብሏል።

ዶክተሩ ግን የሱ ነፃ መሆን በቂ ነውም እያለ ነው።

የ38 አመቱ ዶክተር በጋምስቶን ነቲንግሃምሻየር ነዋሪ ሲሆን የደም አይነቱም እንደልብ የማይገኝ ኤቢ (+) አይነት ነው።

"የማይረባና ትርጉም የሌለው ህግ ነው፤ ለልገሳም እክል ፈጥሯል" ብሏል።

"እንደኔ አይነት ሰዎችን ደም መለገስ አትችሉም ብሎ በህግ ከልክሎ አፍሪካውያን ለጋሾች ደም እየሰጡ አይደለም ማለት ትክክል አይደለም። ችግሩ ከኛ ሳይሆን ከከለከለን ስርአት ነው። ኤንኤችኤስ ህጉን ቀይሮ በርካታ ሰዎች እንዲለግሱ እድል መስጠት አለበት" ይላል።

ኤንኤችኤስ ህጉን ለመከለስ ማሰቡንም የሚበረታታ ነው ብሎታል ዶክተሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤንኤችኤስ ከዚህ ቀደም ጥቁር ደም ለጋሾች ደም ለግሱ በማለት በተደጋጋሚ ጥሪም ከዚህ ቀደም አድርጓል። ለዚህም ምክንያቱ በርካታ ጥቁሮች እንደ ልብ የማይገኝ የደም አይነት ስላላቸው ነው።

የባለቤቱ የደም ውጤት ከኤችአይቪ ነፃ መሆኑንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የዶክተር ፍራንሲስን ሁኔታ እየገመገመው መሆኑንም ኤንኤችኤስ አሳውቋል።

የኤንኤችኤስ አማካሪ ሱ ብራሊስፎርድ በበኩላቸው ደም መለገስ ያለበት ማን ነው የሚለው ጥያቄ የተመሰረተው ደም ለሚቀበሉ ሰዎች የሚኖርባቸውን ስጋትን ለመቀነስ ነው ብለዋል።

"የእያንዳንዱን ግለሰብ ሁነታ በማጤን እንደ ዶክተር ፍራንሲስ ያሉ ሰዎች ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ደም የሚለግሱበት መንገድ እንደሚከፍት እናምናለን" ያሉት አማካሪዋ "በአሁኑ ወቅት ፖሊሰውን በጥልቀት ማየት የሚያስችለንም እቅድ አውጥተናል። አመቱም ሳያልቅ ግምገማችንን እንጀምራለን ብለን እናስባለን"