ናይጄሪያ፡ የ13 አመቱ ታዳጊ እምነቱን በማዋረድ ተከሶ መታሰሩ ውግዘት አስከተለ

የሻሪያ ፍርድ ቤት

የፎቶው ባለመብት, AFP

በናይጄሪያ የ13 አመት ታዳጊ እምነቱን አቆሽሿል እንዲሁም አዋርዷል በሚል ክስ መታሰሩን የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ አውግዞታል።

ድርጅቱ የታዳጊው ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ አሳስቦኛል ብሏል።

ኦማር ፋሩቅ የተባለው ታዳጊ ባለፈው ወር ላይ ነው የአስር አመት እስርና የጉልበት ሰራ ፍርድ የተወሰነበት።

ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው በሰሜን ናይጄሪያ ካኖ ግዛት የሚገኝ የሻሪያ ፍርድ ቤት ነው።

"ውሳኔው ፍፁም ስህተትና ወንጀል ነው። ናይጄሪያም ሆነ የካኖ ግዛት የተቀበለቻቸውን አለም አቀፍ የህፃናት መብትና ደህንነት ድንጋጌዎች የሚጥስ ነው" በማለት በናይጄሪያ የዩኒሴፍ ተወካይ ፒተር ሃውኪንስ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ናይጄሪያ በጎሮጎሳውያኑ 1991 ያፀደቀችውን የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መብት ኮንቬሽኖችንም የሚጥስ የፍርድ ውሳኔ ነው በማለትም ዩኒሴፍ በመግለጫው አትቷል።

ለናይጄሪያ የፌደራልና የተለያዩ ግዛቶች ባልስልጣናት ውሳኔውን አጢነው እንዲቀለብሱትም ዩኒሴፍ ጥሪውን አቅርቧል።

በጎርጎሳውያኑ 1999 የናይጄሪያ ሲቪል አመራር መምጣቱን ተከትሎ በርካታ የአገሪቱ ግዛቶች የሻሪያ ህጎችን ተቀብለዋል።

የሻሪያ ፍርድ ቤቶች እምነታቸው ሙስሊም የሆኑ ሰዎችን ጉዳይ ብቻ ሲሆን የሚያዩት፤ ጉዳዪ በሙስሊምና የእስልምና እምነት ተከታይ ባልሆነ ግለሰብ ከሆነ ግለሰቡ ጉዳዩ በየትኛው ፍርድ ቤት ይታይ የሚለው ላይ ምርጫ አለው።

የእስልምና እምነት ተከታይ ላልሆኑም የተፃፈ ፈቃድ ለሻሪያ ፍርድ ቤት ሊሰጡ ይገባል።