ከእሥር ነፃ ያወጣችውን ሰው ያገባችው የቅርጫት ኳስ ኮከብ

የአሜሪካ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ውድድር ኮከቧ ማያ፤ ከጆናታን አይረንስ ጋር ጋብቻ መሥርታለች

የፎቶው ባለመብት, @mooremaya

የአሜሪካ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ውድድር ኮከቧ ማያ፤ ከጆናታን አይረንስ ጋር ጋብቻ መሥርታለች።

የሁለቱ ሰዎች ጋብቻ ከወትሮው ዜና ለየት ያለ ነው።

ሰውዬው በሃሰት ተወንጅሎ ከርቸሌ ተወርውሮ ነበር። ሰው ደብድበሃል እንዲሁም ዘርፈሃል ተብሎ ነበር ጆናታን የታሠረው።

ጆናታን 23 ዓመት ሙሉ እሥር ቤት ከማቀቀ በኋላ ባለፈው ሐምሌ ነው የተፈታው።

ለዚህ ደግሞ የቅርጫት ኳስ ኮከቧ ማያ እጅ አለበት።

ስፖርተኛዋ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በሃሰት የተወነጀለውን ግለሰብ ከእሥር ለማስለቀቅ ደፋ ቀና ማለት የጀመረችው።

ለዚህም እንዲረዳት በማሰብ የቅርጫት ኳስ ጨዋታዋን ገታ አድርጋ ነበር።

"ከጥቂት ወራት በፊት ነው የተጋባነው። አዲሱን የሕይወታችንን ምዕራፍ በደስታ እያጣጣምን ነው" ስትል ማያ 'ጉድ ሞርኒንግ አሜሪካ' ለተሰኘው የብሔራዊው ኤቢሲ ቴሌቪዥን ጣብያ ዝግጅት ተናግራለች።

የ31 ዓመቷ ማያ ሙር ሚኒሶታ ሊኒክስ ለተባለው ቡድን አራት ጊዜ ዋንጫ ማስገኘት ችላለች።

በ2014 የውድድር ዘመን ደግሞ የዓመቱ ወደር የሌላት ተጫዋች [ኤምቪፒ] ሆና ተሸልማለች።

ማያ በአሜሪካ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ታሪክ እጅግ ድንቅ ከሚባሉ ተርታ ትሰለፋለች።

ሃገሯ አሜሪካን ወክላ ሁለት የኦሎምፒክ ሜዳሊያና ሁለት የዓለም ሻሚፒዮና ወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2019 ባለቤቷ አይረንስን ከእሥር ለማስለቀቅ ስትል ፕሮፌሽናል የቅርጫት ኳስ ሕይወቷን ገታ አድርጋ ነበር።

ጥንዶቹ የተዋወቁት ከ12 ዓመታት በፊት ሲሆን ባለቤቷ አይረንስ የ50 ዓመት ፍርድ ነበር የተፈረደበት።

በሃሰት የተወነጀለውን ግለሰብ ከእሥር ነፃ ነው ሲሉ የበየኑት ዳኛ የክስ መዝገቡን "ደካማና ያልተሟላ" ሲሉ ገልፀውታል።

ማያ፤ የ40 ዓመቱ ባለቤቷ አይረንስ ከእሥር ቤት ሲወጣ ተንበርክካ ነበር የተቀበለችው።

ሰውዬው፤ ሚዙሪ ውስጥ ከሚገኘው ከጄፈርሰን ማረሚያ ቤት ከ23 ዓመታት በኋላ ነፃ ተብሎ ወጥቷል።

አሁን ወደ ቅርጫት ኳስ ሕይወቷ ትመለስ እንደሆን የተጠየቀችው ማያ "ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት" የሚል ምላሽ ሰጥታለች።

"አሁን ይህን ለረዥም ጊዜ የታገልኩትን ትግል በድል በመወጣቴ አረፍ ብዬ መተንፈስ ነው የምፈልገው" ብለላች ኮከቧ ማያ።