የዝነኛዋ የጥቁር መብት ታጋይ ጀግኒት ሮዛ ፓርክስ መኖርያ ቤት ለዕይታ ቀረበ

የሮዛ ፓርክስ ቤት

የፎቶው ባለመብት, EPA

በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በአሜሪካ የጥቁር መብት ተጋድሎ ውስጥ ስሟ ከፍ ብሎ የሚነሳው የጀግኒት ሮዛ ፓርክስ መኖርያ ቤት በጣሊያን ኔፕልስ ሮያል ፓላስ ውስጥ ለዕይታ ቀርቧል፡፡

ጀግኒት ሮዛ ፓርክስ በአለባማ ግዛት በ1955 ከሥራ ወደ ቤቷ አውቶቡስ ተሳፍራ ስትመለስ ለነጭ ወንበሯን እንድትለቅ ስትጠየቅ እምቢኝ በማለቷ ታሪክ መሥራት ችላለች፡፡

ከዚህ እምቢተኝነቷ በኋላ ከአክራሪ የነጭ አሜሪካዊያን የሞት ዛቻ ስለደረሳት መኖርያዋን ከመንገመሪ ወደ ሰሜናዊ አሜሪካ ሚቺጋን፣ ዲትሮይት አዘዋውራ ነበር፡፡

በዲትሮይት ከዘመዶቿ ጋር ትኖርበት የነበረው አነስተኛ የእንጨት/ ጣውላ ቤት ነበር፡፡

ይህ ሮዛ ፓርክስ የኖረችበት ቤት ከብዙ የሕግ ሙግት በኋላ ከአሜሪካ ወደ ጣሊያን ተዛውሮ ነው አሁን ለሕዝብ በመታየት ላይ ያለው፡፡

የአሜሪካ ኮንግረስ ጀግኒት ሮዛ ፓርክስን ‹‹የጥቁሮች መብት ቀዳማዊት እመቤት›› ሲል ነው የሚያሞካሻት፡፡

ያኔ፣ በታኅሣሥ 1፣ 1955 የአላባማ ግዛት ዋና ከተማ መንገምሪ የአውቶቡስ ወንበሯን ለፈረንጅ እንድትለቅ በተጠየቀች ጊዜ አሻፈረኝ በማለቷ ለእስር ተዳርጋ ነበር፡፡

የሷ እምቢተኝነት ያቀጣጠለው አመጽ እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር የመሩትን አውቶቡስ ያለመሳፈር ተቃውሞን ቀሰቀሰ፡፡

ይህ ሰላማዊ ተቃውሞ ጥቁሮች ከሥራ ወደ ቤት፣ ከቤት ወደ ሥራ ሲሄዱ አውቶቡስ እንዳይሳፈሩና ከዚያ ይልቅ በእግር እንዲንቀሳቀሱ ወይም ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ ነበር፡፡ ይህም ውጤት አስገኝቶ የአውቶቡስ ባለቤቶችን ለኪሳራ ዳርጓቸዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጥቁሮች የአውቶቡስ ወንበራቸውን ለነጮች እንዲለቁ የሚያዘው ሕግ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ይህም በአሜሪካ የዘር መድሎ ትግሉ ውስጥ ግዙፍ ድል ያመጣ ክስተት ነበር፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይቺ ጀግኒት ሮዛ ፓርክስ የኖረችባት ቤት በ2008 የዲትሮይት ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለልማት ሊያፈርሳት አቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን የሮዛ ፓርክስ የወንድሟ ሴት ልጅ ሮሂ ማካሊ ቤቱን በ500 ዶላር ገዝታ ለአርቲስት ራየን ሜንዶዛ በስጦታ መልክ አስተላልፋዋለች፡፡

አርቲስት ራየን በበኩሉ ቤቱ እንዳይፈርስ በሚል እንቅስቃሴ ቢያደርግም ስላልተሳካለት የመኖርያ ቤቷን ከፊል ገጽታ ነቅሎ በ2016 ወደ በርሊን በመውሰድ በራሱ ስቱዲዮ ውስጥ ለሕዝብ እንዲታይ አድርጓል፡፡

በ2018 የሮድ አይላንድ ብራውን ዩኒቨርስቲ ቤቱን ለአውደ ርዕይ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ገልጾ ነበር፡፡ ሆኖም ከሮዛ ፓርክስ ቤተሰብ በገጠመው የሕግ ክርክር ሐሳቡ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በመጨረሻ አርቲስቱ ራየን ሜንዶዛ ቀድሞ ይሰራበት ከነበረው ሞራ ግሪኮ ፋውንዴሽን ጋር ግንኙነት በመፍጠር ቤቱ በጣሊያን፣ ኔፕልስ ሮያል ፓላስ ውስጥ ለአውደ ርዕይ እንዲቀርብ አስችሏል፡፡

በአውደ ርዕዩ ላይ አንድ ሙዚቃ ለ8 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ ደጋግሞ እንዲጫወት ተደርጓል፡፡ ይህም ባለፈው ግንቦት ፖሊስ አንገቱን ቆልፎ ለገደለው ጆርጅ ፍሎይድ መታሰቢያ እንዲሆን ነበር፡፡

ጆርጅ ፍሎይድ ‹‹መተንፈስ አልቻልኩም›› እያለ በነጭ ፖሊስ ማጅራቱ ተቆልፎ የተያዘው ለ8 ደቂቃ ከ46 ሰኮንድ ነበር፡፡

ጆርጅ ፍሎይድ ከተገደለ ወዲህ ተመሳሳይ ዘረኛ ግድያዎች እዚያም እዚህም የተሰሙ ቢሆንም የጥቁሮች የነጻነትና የእኩልነት ትግል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነቃቃትን አሳይቷል፡፡

ጆርጅ ፍሎይድን ማጅራቱን ቆልፎ የገደለው ነጭ ፖሊስ መኮንን ዴሪክ ቾቪን ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር፡፡