አሜሪካ፡ የኖቶሪየስ ቢአይጂ ዘውድና የቱፓክ የፍቅር ደብዳቤዎች በጨረታ ተሸጡ

የኖቶሪየስ ቢአይጂ ዘውድ

የፎቶው ባለመብት, Sotheby's

ታዋቂው አሜሪካዊ ራፐር ኖቶሪየስ ቢአይጂ መጨረሻ ላይ በፎቶ የታየበት ዘውድ 600 ሺህ ዶላር፣ 22.5 ሚሊዮን ብር ተሸጧል።

ራፐሩ ከመሞቱ ሶስት ቀን በፊት አድርጎት ነበር የተባለው የፕላስቲክ ዘውድ "የኒውዮርኩ ንጉስ" (ኪንግ ኦፍ ኒውዮርክ) የሚል ስያሜ በተሰጠው ፎቶም ላይ ታይቷል።

ዘውዱ በመጀመሪያ 300 ሺህ ዶላር ተገምቶ ነበር። ሆኖም በ600 ሺህ ዶላር ሂፕ ሆፕ እቃዎች ላይ ባተኮረው ጨረታ ተሽጧል።

ጨረታው ቱፓክ ሻኩር በ16 አመቱ የፃፋቸው የፍቅር ደብዳቤዎችንም አቅርቧል።

"ጣፋጭ የሆኑ ቃላትን ያዘሉ" ደብዳቤዎች የተባሉ ሲሆን ቱፓክ በእጁ የፃፋቸው 22 ደብዳቤዎችን አካቷል።

እነዚህም ደብዳቤዎች በ75 ሺህ 600 ዶላር መሸጣቸው ተገልጿል።

ምንም እንኳን "የኒውዮርኩ ንጉስ" ፎቶ ታዋቂ ቢሆንም ይህን ያህል ገንዘብ ያወጣል የሚለውን ማንም አልገመተውም።

በወቅቱ የራፐሩ ስራ አስኪያጅ የነበረውና ፎቶው ሲነሳ በነበረበት ወቅት አብሮት የነበረው ራፐሩ ዲዲ 'ከሂፕ ሆፕ ንጉስ በላይ የበርገር ንጉስ ትመስላለህ እያለው ነበር"።

ዘውዱ በፎቶ ባለሙያው ባሮን ክላይቦርና በራፐሩ የተፈረመ ነው። ቢአይጂ በጎሮጎሳውያኑ 1997 ነው በሽጉጥ የተገደለው።

ጨረታውን የሚያካሂደው ድርጅት ሶቴቢ ዋና አማካሪ ካሳንድራ ሃቶን ለሮይተርስ እንደተናገሩት ዘውዱ "በሂፕ ሆፕ ታሪክ ውስጥ የሚታወቅ ምልክት ነው" ብለዋል።

" በተለያዩ አገራት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ይህንን ዘውድ ያውቁታል። በቲሸርቶች ላይ፣ በቡና መጠጫ ኩባያ እንዲሁም በሻማ ይታያል። በጣም ትልቅ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቱፓክ የፍቅር ደብዳቤዎች በ1980ዎቹ በባልቲሞር የጥበብ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት ካቲ ሎይ ለምትባል ግለሰብ የላከው ነው።

ከካቲ ጋር ለሁለት ወራት ያህልም የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል።

በደብዳቤዎቹም ላይ ለሷ ያለውን ጥልቅ ፍቅር፣ ግንኙነታቸውን በማቋረጧ የተሰማውን ስሜት እንዲሁም ከአመት በኋላ እንዲሁም ፀፀቱን አስፍሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቱፓክ በደብዳቤው መደምደሚያ ላይ "ፍቅር ቱፓክ"፣ "እስከ ዘለአለሙ ድረስ ቱፓክ"፣ "ከልብ ከመነጨ ፍቅር ጋር ቱፓክ"፣ "ሁልጊዜም የአንቺው ቱፓክ" የሚሉ ሃረጎችንም ነው መሰናበቻ ያደረጋቸው።

ደብዳቤዎቹ ራፐሩ ልበ ስስ እንደነበርና እምቢይ መባልን የሚፈራ ሰው እንደነበር አሳይቷል።

ስመ- ጥሩው፣ የግጥም ድንቅ ችሎታ የነበረው ቱፓክ የተገደለው በላስቬጋስ በጎሮጎሳውያኑ 1996 ነበር።

ከሚያልፍ መኪና በተተኮሰበት ጥይት ነው ህይወቱ ያለፈው። ዕድሜውም 25 ነበር።

ከጨረታው የሚገኘው የተወሰነው ገቢ በኒውዮርክ ለሚገኙ የማህበረሰቡ ፕሮጀክቶች እንደሚውልም ተገልጿል።