ባርቤዶስ የእንግሊዟን ንግስት ኤሊዛቤትን ከርዕሰ ብሔርነት ልታነሳ ነው

ንግስት ኤልሳቤጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ባርቤዶስ የእንግሊዟን ንግስት ኤሊዛቤትን ከርዕሰ ብሔርነት አንስታ ሪፐብሊክ ለመሆን ማቀዷን አስታወቀች።

"የቅኝ ግዛት ታሪካችንን እርግፍ አድርገን የምንጥልበት ሰዓት መጥቷል" ብሏል የካሬቢያን ደሴቷ ሃገር መንግሥት።

ሃገሪቱ ኅዳር 2014 ለምታከብረው የነፃነት በዓል [ከእንግሊዝ ግዛት ነፃ የወጣችበት] ሙሉ በሙሉ ሪፐብሊክ የመሆን ዕቅድ አላት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ በመግለጫቸው እንዳሉት ሃገሪቱ ባርቤዶሳዊ ርዕሰ ብሔር ያስፈልጋታል።

"ጊዜው እኛ ማን እንደሆንና ምን ማድረግ እንደምንችል በልበ ሙሉነት የምናሳይበት ነው" ይላል የጠቅላይ ሚኒስትሯ ፅሑፍ።

የብሪታኒያው ባኪንግሐም ቤተ መንግሥት ጉዳዩ የባርቤዶስ ሕዝብና መንግሥት ነው ብሏል።

ለቤተ መንግሥቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ውሳኔው "ከምድር የመነጨ አይደለም" ከዚህ በፊትም ቢሆን በይፋ ሲነገር የቆየ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስለባርቤዶስ ጥቂት እውነታዎች

• ከብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችው በአውሮፓውያኑ 1966 ነው

• ከካሬቢያን ደሴቶች የበለፀገችና በሕዝብ ብዛት አንደኛ ናት

• የእንገሊዟ ንግሥት ኤሊዛቤት የሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር ናቸው

• በስኳር ምርት የምታተወቀው ሃገር የቱሪዝምና ፋይናንስ መናገሻ ናት

• ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ በአውሮፓውያኑ 2018 ሥልጣን ሲይዙ የመጀመሪያዋ ሴት መሪ ሆነው ነው

ባርቤዶስ ውሳኔዋን ያሳወቀችው መንግሥት ለሚቀጥለው ዓመት ምን ዓይነት ፖሊሲዎች እንደያዘ ይፋ ባደረገበት የፓርላም ስብሰባ ላይ ነው።

ባርቤዶስ ከንጉሣዊ የመንግሥት አስተዳደር ተላቃ የራሷን መንገድ እንድትከተል ጥያቄዎች መቅረብ ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ከካሬቢያን ሃገራት ከእንግሊዝ ቅኝ ነፃ ከወጣች በኋላ የራሷን መንግሥት የመሠረተችው የመጀመሪያዋ ሃገር ጉያና ናት።

ከዚያ ቀጥሎ ትሪኒዳድ እና ቶቤጎ እንዲሁም ዶሚኒካ ከእንግሊዝ ንጉሣዊ አገዛዝ ሥርዓት ራሳቸውን ያወጡ ሃገራት ናቸው።

ቢሆንም ሁሉም ሃገራት ኮመንዌክዝ የተሰኘው የቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሃገራት የተሰባሰቡበት ማሕበር አባላት ናቸው።

ባርቤዶስ የቅኝ ግዛት ታሪኬን እሽራለሁ ማለቷ ሌሎች የካሬቢያን ሃገራትን ሊያነሳሳ የሚችል እንደሆነ ግምት አለ።

የእንግሊዟ ንግሥት ኤሊዛቤት በአሁኑ ወቅት የ15 ሃገራት ርዕሰ ብሔር ናቸው።