የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን በቃኝ አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አልሲራጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሊቢያ ሁለት መንግሥት ነው ያለው፡፡ አንዱ በምሥራቅ ሊቢያ የሚንቀሳቀሰው የኸሊፋ ሐፍጣር መንግሥት ሲሆን ሁለተኛው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና ያለው መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገው አስተዳደር ነው፡፡

የዚህ አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አልሲራጅ በቅርቡ ሥልጣኔን አስረክባለሁ ብለዋል፡፡

አልሲራጅ ሥልጣናቸውን ለተተኪ የሚያስረክቡት በመጪው ጥቅምት ወር ላይ ነው፡፡

አልሲራጅ ይህን ያስታወቁት በቴሌቪዥን ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

የአልሲራጅ እቅድ በመጪው ወር በጄኔቫ ተፎካካሪዎች በሚያደርጉት ስብሰባ መንግሥቱን የሚመራ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመረጥ ነው፡፡

የአልሲራጅ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውስጡ ባሉ የትሪፖሊን አስተዳደር ከመሰረቱት ተፋላሚ ወገኖች ከባድ ጫና ሲደርስበት ነበር፡፡

ሕዝቡም ኑሮ ከብዶት ፣ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ባለመሆኑ በመንግሥት ላይ ተቃውሞውን ሲያሰማ ቆይቷል፡፡

ፋይዝ አልሲራጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እገዛ በተቋቋመውና ሞሮኮ፣ ሺህራት ከተማ ላይ በ2015 ዓ.ም እውን በሆነው የሽግግር ካውንስል አማካኝነት ነበር፡፡

ሆኖም ከዚህ ስምምነት በኋላ ሊቢያ ሰላሟ አልተመለሰም፡፡ በእርግጥ የሙአመር ጋዳፊ ሞትን ተከትሎ ባለፉት 9 ዓመታት ሊቢያ ስትታመስ ነው የኖረችው፡፡

የአልሲራጅ መንግሥት በኳታርና በቱርክ ሰፊ ድጋፍ የሚያገኝ ሲሆን ተቀናቃኙን የጦር ጄኔራል ኸሊፋ ሐፍጣርን ሩሲያን ጨምሮ ብዙዎቹ የገልፍ አገራት እንዲሁም ግብጽ ያስታጥቁታል፡፡ ፈረንሳይም ውስጥ ውስጡን የጄኔራሉ ቀኝ እንጅ እንደሆነች ይነገራል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሩሲያ ጋር በሊቢያ ጉዳይ ተማክረንበታል፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይም ደርሰናል ብለዋል ትናንት፡፡

ቱርክና ሩሲያ በሶሪያ እንዳደረጉት ሁሉ በሊቢያም ጡንቻቸውን ይለካካሉ የሚል ስጋት አይሎ ነበር፡፡ በተለይም ሩሲያ ለሶሪያ የተጠቀመቻቸውን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ወደ ምሥራቅ ሊቢያ ማስገባቷ ከተሰማ ወዲህ ቱርክም ወታደሮቿን ወደ ትሪፖሊ ልካ ነበር፡፡

ይህ ሁኔታ ሊቢያን ቀጣይዋ ሶሪያ ያደርገጋታል የሚል ፍርሃት እንዲነግስ አስችሎ ነበር፡፡

በሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎች አሁንም በከፊል ጦርነት፣ በከፊል የጦር አቁም ስምምነትና በከፊል ድርድር ውስጥ እየዋለሉ ይገኛሉ፡፡