የናይጄሪያዋ ግዛት ደፋሪዎች እንዲኮላሹ በህግ ፈቀደች

መደፈርን ሊቃወሙ የወጡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የናይጄሪያዋ ካዱና ግዛት ደፋሪዎች በህክምና እንዲኮላሹ ህግ አፅድቃለች።

የግዛቷ አስተዳዳሪ ናስር አህመድ ኤል ሩፋይ ባለፈው ሳምንት የቀረበላቸውን ረቂቅ ህግ በትናንትናው እለት በመፈረም አፅድቀውታል።

ህጉ ከአስራ አራት አመት በታች ያሉ ህፃናትን የደፈሩ እንዲኮላሹ ብቻ ሳይሆን የሞት ፍርድንም አካቷል።

የተደፈሩት ደግሞ ከአስራ አራት አመት በላይ ከሆኑ በህክምና እንዲኮላሹ እንዲሁም የእድሜ ልክ እስራት ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ህፃናትን የሚደፍሩ ሴቶችም ቢሆኑ የማህፀን ቱቧቸው እንዲወገድ የሚደረግ ሲሆን የሞት ቅጣትም በተጨማሪ ተካቶበታል።

የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው ከአስራ አራት አመት በታች ያሉ ህፃናት በአባሪነት የህክምና ሪፖርት ማምጣት ይኖርባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ህፃናትን የሚደፍሩ ሰዎች ዝርዝርም በሚዲያ እንደሚወጣና ለህዝቡም ይፋ ይሆናል ተብሏል።

የግዛቲቱ አስተዳዳሪ በትናንትናው ዕለት ረቂቅ ህጉ ላይ መፈረማቸውንና ህግ ሆኖም እንደፀደቀ ያስታወቁት በትዊተር ገፃቸው ነው።

በናይጄሪያ ካሉ ግዛቶች መካከል እንዲህ አይነት ህግ በማፅደቅ ካዱና ቀዳሚ ሆናለች።

የናይጀሪያ ፌደራል መንግሥት ደፋሪዎችን ከአስራ አራት አመት እስከ እድሜ ልክ እስራት ቢቀጣም ግዛቶች ግን የራሳቸውን ህግ ማውጣት ይችላሉ።

የተደፈሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በማህበረሰቡ ካለው ተጠቂዎችን ጥፋተኛ ከማድረግ እሳቤ አንፃር ብዙዎች ደፍረው ወደ ህግ ቦታ አይሄዱም።

ደፍረው ሪፖርት ያደረጉትም ቢሆን ክስ ተመሰርቶ የሚፈረድባቸውም ጥቂቶች ናቸው።

በሰኔ ወር ላይ በርካታ የናይጄሪያ ግዛት አስተዳዳሪዎች እየጨመረ የመጣውን የሴቶች መደፈርና ጥቃት አስመልክቶ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተላልፈው ነበር።

በናይጄሪያ ከጎርጎሳውያኑ 2015 ጀምሮ የተፈረደባቸው 40 ደፋሪዎች ብቻ እንደሆኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

አገሪቷም ህጓን አሻሽላለች።

የመድፈር ክስን አስቸጋሪ የሚያደርገው አቃቤ ህግ ማስረጃ ማምጣት ስለሚኖርበት አድካሚና ቴክኒካል ጉዳዪ የተወሳሰበ እንደሚያደርገው ይነገራል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የተጣለው የእንቅስቃሴ መገደብም የሚደፈሩ ሴቶችን ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጎታል።

በሃምሌ ወር የ22 አመት እድሜ ያላት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ተደፍራ መገደሏ ከፍተኛ ቁጣን ፈጥሯል።

ይህንንም ተከትሎ ናይጄሪያውያን ንዴታቸውን ለመግለፅ ጎዳና ላይ ወጥተዋል፤ 'ዊ አር ታየርድ' (ደክሞናል) በሚልም በትዊተር ላይ ዘመቻ ተጀምሮም ነበር።

በርካቶችም የሞት ቅጣትን ጨምሮ ጠበቅ ያለ ህግ እንዲወጣም ጠይቀዋል።

በህክምና የማኮላሸት ቅጣት በአንዳንድ አገራት ተግባራዊ ቢሆንም አወዛጋቢ ነው።