አቶ ልደቱ ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ክስ ቀረበባቸው

አቶ ልደቱ አያሌው

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው የፓርቲው ፕሬዝደንት ለቢቢሲ አረጋገጡ።

አቶ አዳነ እንዳሉት በዛሬው ዕለት የአቶ ልደቱ ጉዳይ ከዚህ በፊት ሲታይ ከነበረበት የቢሾፍቱ ከተማ በመውጣት በአዳማ ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት እንደታየ ጠቅሰው ይህንንም የሰሙት ትናንት ማታ መሆኑን ገልጸዋል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ክስ የቀረበባቸው ልደቱ አያሌው ላይ ዐቃቤ ሕግ የጦር መሳሪያ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 3ን በመተላለፍ ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ መከሰሳቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም ዘግበዋል።

አቶ ልደቱ ከዚህ በፊት በቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሲታይ ቆይቶ የቀረበባቸውን የምርመራ መዝገብ ቢዘጋውም ከእስር በነጻም ሆነ በዋስ ለመውጣት ሳይችሉ በእስር ላይ ቆይተው ሌላ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ነገር ግን የፓርቲው ፕሬዝደንት አቶ አዳነ ታደሰ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደብዳቤው ከወጣ በኋላ ትላንት [ረቡዕ] ምሽት ነው አቶ ልደቱ አዲስ ክስ እንደተመሠረተባቸው የተሰማው።

"የቢሾፍቱ ፍርድ ቤት ነፃ ናቸው ናቸው ብሎ አሰናብቷቸው ነበር። እኛም በጠበቆቻችን አማካይነት ይግባኝ ጠይቀን ነበር። ነገር ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተፈፃሚ ሊሆን ስላልቻለ አቶ ልደቱ በትላንታው ዕለት ጠበቆቻቸውን 'እስካሁን ለረዳችሁኝ አመሰግናለሁ' ብለው አሰናብተዋቸዋል።"

አቶ ልደቱ ትናንት [ረቡዕ] ጉዳያቸውን ይዘው ሲከታተሉ የነበሩትን ጠበቆቻቸውን ማሰናበታቸውን በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀው ነበር። በዚህም ጉዳያቸው እየታየበት ባለው ሂደትቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው በማሳወቅ ነው ጠበቆቻቸውን እንዳሰናበቱ የገለጹት።

አቶ ልደቱ በደብዳቤያቸው ላይ እንዳሉት ባለፉት ስምንት የችሎት ሂደቶች ላይ የፖሊስና የዐቃቢ ሕግ ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ሲያገኙ መመልከታቸውን ጠቅሰው "የእኔ ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎች ግን አንድም ጊዜ ተቀባይነት ሲያገኙ አልታዩም" በማለት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱበትን ምክንያት ገልጸዋል።

በፖለቲካ አመለካከታቸው ለእስር እንደተዳረጉ የገለጹት አቶ ልደቱ "በፖለቲካ አመለካከቴ እንድታሰር የወሰኑብኝ የፖለቲካ ሰዎች ስለወደፊቱ እድሌም የሚወስኑትን የፖለቲካ ውሳኔ በእስር ላይ ሆኜ እየተጠባበኩኝ እገኛለሁ" ብለዋል።

ለእስራቸውም ቀደም ሲል ያዘጋጁት የሽግግር መንግሥት ምስረታ ሰነድና በታትሞ ያልተሰራጨው አዲሱ መጽሐፋቸው ምክንያቶች እንደሆኑ በማመን "በአጭሩ እኔ የታሰርኩት ለምን ወንጀል ፈጸምክ ተብዬ ሳይሆን ለምን አሰብክ ተብዬ ነው" ነው ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ "ሕግ የፖለቲካ መሳሪያ በሆነበት ሁኔታ በሕግ ክርክር መብትን ማስከበር ስለማይቻል ከአሁን በኋላ ሕጋዊ ግዴታዬን ለመወጣት ቀጠሮ ሲሰጠኝ በችሎት ፊት ከመገኘት ባለፈ የሕግ ክርክር የማድረግ ፍላጎት የለኝም" ሲሉ ጠበቆቻቸውን አመስግነው ማሰናበታቸውን አመልክተዋል።

የኢዴፓ ፕሬዝደናት አቶ አዳነም ለቢቢሲ "አቶ ልደቱ በፍትህ ሂደቱ ከዚህ በኋላ እምነት የለኝም። የመከራከርም ፍላጎት የለኝም ሲሉ ነው። ውሳኔው ፖለቲካዊ ስለሆነ ፖለቲካዊ መፍትሄ እስኪሰጠኝ ድረስ እሥር ቤት እቆያለሁ ብለው ነው ያሰናበቷቸው" ብለዋል።

የአቶ ልደቱ ጠበቃቸውን የማሰናበታቸውን ውሳኔ የሚገልጸው ደብዳቤ ይፋ መሆኑን ተከትሎ አዲስ ክስ እንደተመሠረተባቸው መስማታቸውን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል።

"እኛ ከቢሾፍቱ ወደዚህ [አደስ አበባ] እንደመጣን አዳማ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደመሠረተባቸው ተነግሮናል። ዛሬ [ሐሙስ] 4፡00 ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደዚያ እያመራሁ ነው" ሲሉ ጉዳዩን ለመከታተል እያመሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ጨምረውም አቶ ልደቱ አያሌው ትናንት [ረቡዕ] ማታ 1፡30 ላይ የክፍላቸው በር ተንኳኩቶ 'ለጠዋት ተዘጋጅ ነገ [ሐሙስ] አዳማ ላይ ቀጠሮ አለህ' ተብሎ እንደተነገራቸው አቶ አዳነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ልደቱ የተመሠተባቸው ክስ አዲስ እንደሆነና የክሱን ምንነት እስካሁን እንዳላወቁ ፕሬዝደንቱ ያስረዳሉ።

ጠበቆቻቸው አዳማ ይገኛሉ?

ምንም እንኳ አቶ ልደቱ ጠበቆቻቸውን ቢያሰናብቱም አዳማ ፍርድ ቤት በሚሰማው ክስ ላይ ጠበቆች እንደሚገኙ አቶ አዳነ ይናገራሉ።

"አቶ አብዱልጀባር [ጠበቃ] ምን እንኳ ደብዳቤው ቢደርሰኝም ቋንቋውን በማያውቁበትና ክሱ ላይ ያለውን ጭብጥ በደንብ መረዳት በማይችሉበት ሁኔታ ትተናቸው አንሄድም። ስለዚህ እሳቸው ቢከለክሉኝም ዛሬ እገኛለሁ ብለውናል። ስለዚህ ወደዚያ [አዳማ] እየሄድን ነው።"

አቶ ልደቱ ዛሬ አዳማ ላይ ከሚቀርብባቸው ክስ አስቀድሞ ጠበቆቻቸውን ሲያሰናብቱ 'እስካሁን ድረስ የተጓዝኩት ጉዞ በፖለቲካ መያዜን የሚያረጋግጥ ነው። ይህን ማረጋገጥ ከቻልኩ ለኔ በቂዬ ብለው' ተስፋ እንደቆረጡ የአዴፓ ፕሬዝደንት ይናገራሉ።

አቶ አዳነ "በአዳማው የፍርድ ሂደትም ቢሆን የሚለወጥ ነገር ይኖራል ብለን አናምንም" ይላሉ። ነገር ግን በምን ዓይነት ሁኔታ ነገሮችን እናስኪድ የሚለውን ከሱ [አቶ ልደቱ] ጋር ተመካክረን የምናደርግ ይሆናል ባይ ናቸው።

አቶ ልደቱን ለእሥር የተዳረጉት ከጥቂት ወራት በፊት በቢሾፍቱ ከተማ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በማስተባበርና በመደገፍ ተጠርጥረው እንደሆነ ይታወሳል።