የትግረይ ምርጫ ፡ ባይቶና ፓርቲ የተሰጠን አንድ ወንበር አይገባንም አለ

ባይቶና ሊቀ መንበር

በቅርቡ በተካሄደው የትግራይ ክልል ምርጫ ላይ ከተሳተፉት ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ባይቶና አባይ ትግራይ የተሰጠን ወንበር አይገባንም አለ።

ፓርቲው ዛሬ [ሐሙስ] ባወጣው መግለጫ "የምርጫው ፍትህዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ተበላሽቷል" ብሏል።

ምርጫውን ገዢው ፓርቲ ህወሓት ከ98 በመቶ በላይ የመራጮችን ድምፅ በማግኘት እንዳሸነፈ መገለጹ ይታወሳል።

በአዲሱ የክልሉ ምክር ቤት የመቀመጫ ድልድል ሕግ መሠረት ህወሓት ካገኛቸው 152 የምክር ቤት መቀመጫዎች በተጨማሪ 38 ወንበሮች ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ይከፋፈላሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ነገር ግን የምርጫ ኮሚሽኑ ባወጣው ውጤት መሠረት ህወሓት 189 ወንበሮች ሲያገኝ 1 ወንበር ደግሞ ባይቶና ማግኘቱ ተነግሯል።

ነገር ግን ባይቶና ዛሬ ባወጣው መግለጫ "ውሳኔው ባንቀበለውም ሕግን እናከብራለን። በሕጉ መሠረት ደግሞ ይህ ወንበር ለእኛ ይገባናል ብለን አናምንም" ብሏል።

ከትግራይ ክልል ምርጫ በፊት የወጣው ሕግ 20 በመቶ ወንበሮች በተፎካካሪ መካከል የሚከፋፈል ነው ይላል። ነገር ግን ይህ ሕግ በጊዜው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

ፓርቲው በመግለጫው "የትግራይ የምርጫ አዋጅ ከመጀመሪያውም ህወሓትን ለማገልገል የወጣ ነው ብለን እናምናለን" ብሏል።

"ይሁን እንጂ በቀመሩ መሠረት እኛ የደርስንበት የተሰጠን የሕዝብ ድምፅ ወንበር ለማግኘት የሚበቃ እንዳልሆነ ነው" ይላል መግለጫው አክሎ።

ይሁን እንጂ ባይቶና፤ ለእኛ እንደሚገባ የሚያረጋግጥ የሕግ አገባብ ወይም ስሌት ካለ የተሰጠንን ወንበር በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን ይላል።

ፓርቲው የትግራይ ሕዝብ ምርጫውን ለማሳካት ላደረገው አስተዋፅዖ ክብር እንዳለው በመግለጫው አትቷል። አክሎም ለምርጫ ኮሚሽኑ ለክልሉ የፀጥታ ኃይሎችም ምስጋናውን አቅርቧል።

ፓርቲው በምርጫው ቀንና ከምርጫው በኋላ አጋጠመ ያለውን እንቅፋት በተመለከተም መልዕክት አስተላልፏል።

"ማንን እንደመረጣችሁ እናውቃለን"፤ "ከምርጫው በኋላም የት እንደምትገቡ እናያለን"፤ "ምርጫው እስኪያልቅ ድረስ ከተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ጋር እንዳትታዩ" የሚሉ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ማስፈራራቶች ደረሱባቸው ሰዎች እናዳሉ ገልጿል።

አልፎም የህወሓት መዋቅር ቤት ለቤት እየዞሩ ባይቶና ላይ የሠሩት ስም ማጥፋት በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ፓርቲው ገልጿል።

ጳጉሜ 04/2012 ዓ.ም በትግራይ ክልል ምርጫ የተካሄደው ምርጫን በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕጋዊ ያልሆነ እና ተፈጻሚነት የሌለው እንዳለው ይታወሳል።