ሀሪኬን ሳሊ፡ በአሜሪካ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ያለ መብራት አስቀረ

በአልባማ በጎርፍ መካከል የሚሄድ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በተለያዩ አገራት የተፈጥሮ አደጋዎች በርካቶችን ለችግር እየዳረገ ነው። እዚህ እኛ አገርም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጎርፍ ሳቢያ ተፈናቅለዋል፤ ንብረቶችም ወድመዋል።

በአሜሪካም ሳሊ በተባለ ንፋስ በቀላቀለ ዝናብ ሳቢያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ያለ መብራት ቀርተዋል። ለሕይወታቸውም ሰግተዋል።

ሳሊ ባስከተለው በዚህ ከባድ ዝናብና ማዕበል የአሜሪካ ባህር ዳርቻዎች ክፉኛ ተመትተዋል። ቀስ እያለ የሚጓዘው ንፋስ የቀላቀለው ዝናብ ፍሎሪዳና አላባማ ግዛቶችን መምታቱን ቀጥሏል።

በአደጋውም የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በጎርፍ ከተጥለቀለቁ አካባቢዎች እንዲወጡ ተደርገዋል።

በፍሎሪዳ የምትገኘው ፔንሳኮላም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን፤ በጎርፉ የተወሰደ መርከብ በባህሩ ላይ የተገነባውን የቤይ ድልድይን የተወሰነ ክፍል እንዲደረመስ አድርጎታል።

የብሔራዊ ሄሪኬን ማዕከል "ድንገተኛ አደጋ የሚያስከትልና ለሕይወት አስጊ የሆነው ጎርፍ፤ በፍሎሪዳዋ ፓንሃንድል እና ደቡባዊ አላባማ አሁንም እንደቀጠለ ነው" ብሏል።

የፔንሳኮላ የድንገተኛ አደጋ ኃላፊ ጊኒ ክራኖር በበኩላቸው፤ አውሎ ንፋስ የቀላቀለው ይህን ክስተት "በከተማዋ ላይ የ4 ወራትን ዝናብ በአራት ሰዓታት ያወረደ ነው" ሲሉ ለሲ.ኤን.ኤን. ተናግረዋል።

በአላባማ ኦሬንጅ የባህር ዳርቻም በአደጋው አንድ ሰው የሞተ ሲሆን ሌላኛው የደረሰበት አለመታወቁን የከተማዋ ከንቲባ ገልፀዋል። ከንቲባው የሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ግን የለም።

ሳሊ በሰዓት 169 ኪሎሜትር እየተምዘገዘገ በአላባማ ግዛት ባህር ዳርቻዎች የደረሰው ረቡዕ ዕለት ነበር።

እንደ ኤን.ኤ.ኤስ. ከሆነ ሁለተኛው ምድብ ሄሪኬን ያለማቋረጥ ንፋስ ይዞ የሚጓዘው በሰዓት ከ96 እስከ 110 ሜትር ነው።

በዚህ ምድብ የሚገኘው ሄሪኬን፤ በጣም አደገኛ የሆነ ንፋስ ሲሆን በአብዛኛውም በቤቶች እና ጥልቅ ሥር በሌላቸው ዛፎች ላይ ጉዳት ያስከትላል ብሏል ማዕከሉ።

ሳሊ በአትላንቲክ ውቅያኖስ አካባቢ ከሚከሰቱ ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ አንዱ ነው።