ኮሮናቫይረስ ፡ ኮቪድ-19 ኒውዚላንድን ለዓመታት አጋጥሟት ለማያውቅ የኢኮኖሚ ውድቀት ዳርጓታል ተባለ

ኒውዚላንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በተከሰተ በመጀመሪያዎቹ ወራት በርካቶችን እንደ ቅጠል ሲያረግፍ፤ ኒው ዚላንድ ግን በሌሎች የአውሮፓና አሜሪካ አገራት የሆነው አልገጠማትም።

ይህ የሆነው የአገሪቷ መንግሥት ቀድሞ በወሰዳቸው ጥብቅ እርምጃዎች ምክንያት ነው።

ኒው ዚላንድ ለወረርሽኙ ምላሽ በመስጠት ከተወደሱ አገራት መካከል አንዷ ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርንም በዚህ ሥራቸው ተሞግሰዋል።

ነገር ግን አገሪቷ ኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የጣለቻቸው ጥብቅ ገደቦች ባለፉት አስርት ዓመታት አጋጥሟት ወደማያውቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደከተታት ተገልጿል።

በአገሪቷ የእንቅስቃሴ ገደቡ በተጣለባቸውና ድንበር በዘጋችበት ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ባሉት ጊዜያት የኢኮኖሚ እድገቷ በ12̀.2 በመቶ ማሽቆልቆሉ ተገልጿል።

ይህም ኒው ዚላንድ ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ በጎርጎሮሳዊያኑ 1987 ከገጠማት የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ድቀት ነው ተብሏል።.

ይሁን እንጅ መንግሥት ለወረርሽኙ የሰጠው ምላሽ ኢኮኖሚው በፍጥነት ወደማንሰራራት እንደሚያመራው ተስፋ አድርጓል።

5 ሚሊየን የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት ያላት ኒው ዚላንድ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን ያወጀች ቢሆንም አሁንም ግን በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ።

አገሪቷ በቫይረሱ ሳቢያ ያስተናገደችው ሞትም 25 ብቻ ነው።

የኢኮኖሚው ጉዳይም ነሐሴ ወር ላይ ባልተጠበቀ መልኩ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ የተራዘመውና በሚቀጥለው ወር በሚደረገው ምርጫ ላይም ዋነኛ ጉዳይ ሆኖ እንደሚነሳ ይጠበቃል።

የኒው ዚላንድ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ፖል ፓስኮ፤ ወረርሽኙን ተከትሎ ከመጋቢት ወደ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረጉ ገደቦች በተወሰኑ የኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደነበረው ተናግረዋል።

"በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ፣ በሆቴሎችና ሬስቶራንቶች እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ መዳከም ታይቷል። እነዚህ ዘርፎች በዓለም አቀፉ ጉዞ እገዳ እና በአገሪቷ ተጥሎ በነበረው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ በቀጥታ ተጎጅ ሆነዋል" ብለዋል ቃል አቀባዩ ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን መንግሥትም ቫይረሱን በመቆጣጠር የተገኘው ውጤት ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ያግዛል ብለዋል።

የአገሪቷ የገንዘብ ሚኒስትር ግራንት ሮበርትሰን በበኩላቸው፤ የኢኮኖሚ እድገት [ጂዲፒ] አሃዝ ከተጠበቀው የተሻለ መሆኑን በመጥቀስ ወደ ፊት ኢኮኖሚው እንደሚሻሻል አስተያየታቸው ሰጥተዋል።

አንዳንድ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎችም ኒው ዚላንድ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ጠንካራ ምላሽ በመስጠቷ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እንደሚያገግም ተንብየዋል።