እግር ኳስ፡ ሊዮኔል ሜሲ ስሙ የንግድ ምልከት መለያ እንዲሆን ተፈቀደለት

ሊዮኔል ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ተጨዋች ሊዮኔል ሜሲ ስሙን የንግድ ምልክት መለያ እንዲሆን ለማድረግ ፍርድ ቤት ሲከራከር ቆይቷል።

የፍርድ ቤት ክርክሩ የተጀመረው አንድ የስፔን የሳይክል ኩባንያ ከእኔ የንግድ ምልክት ጋር ይመሳሰላል በማለቱ ነበር።

ኩባንያው ማሲ ነው የሚባለው። ታዲያም ሜሲ ከሚለው ጋር ተመሳሳይነት ስላለው በሕዝቡ ዘንድ ውዥንብር ይፈጥራል ሲል ነበር መከራከሪያ ያቀረበው።

የባርሴሎና እግር ኳስ ተጨዋች ሊዮኔል ሜሲ ለስፖርት አልባሳት መለያ ስሙን እንደ ንግድ መለያ አድርጎ ለማስመዝገብ ያመለከተው ከ9 ዓመታት በፊት ነበር። እነዚህን ሁሉ ዓመታትም በክርክር አሳልፏል።

በመጨረሻም ጉዳዩን የተመለከተው የአውሮፓ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እግር ኳስ ተጨዋቹ ሊዮኔል ሜሲ ስሙን እንደ ንግድ ምልክት መለያ ማስመዝገብ እንደሚችል ዛሬ ብይን ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ የስፔን የሳይክል ኩባንያ ማሲ እና የአውሮፓ ህብረት የአዕምሮ ንብረት ጽ/ቤት ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል።

የአውሮፓ የፍትሕ ፍርድ ቤት ሕዝቡ የሁለቱን የንግድ ምልክት መለያዎች ልዩነት መለየት ይችል እንደሆነ በሚመዘንት ጊዜ፤ የኮከብ ተጨዋቹ ዝና ከግምት መግባቱ አይቀርም ብሏል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የአውሮፓ ሕብረት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሁለት ዓመታት በፊት እግር ኳስ ተጨዋቹ ዝነኛ በመሆኑ ውዥምብር ሊፈጥር አይችልም ሲል ያስተላለፈውን ውሳኔ ተቀብሎ ብይን ሰጥቷል።