እስክንድር ነጋ ፡ ከዚህ በፊት 'ለዓመታት ወደታሰሩበት የእስር ክፍል ተመልሰው ገቡ'

እስክንድር ነጋ

አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከዚህ ቀደም ታስረውበት ወደ ነበረው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መዛወራቸውን ጠበቃቸው አቶ ሔኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ገለፁ።

እንደ አቶ ሔኖክ አክሊሉ ከሆነ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌላ አንድ ግለሰብም ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ ላይ አቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር አዋጅን በመተላለፍ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

በፖለቲከኛውና ጋዜጠኛው አቶ እስክንድር ነጋ ላይ የቀረቡት ክሶች ኃይልን በመጠቀም መንግሥትን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራን የሚጠቅሱ ናቸው።

ጳጉሜ 5/2012 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ላይ አቶ እስክንድር ላይ ክስ መመስረቱን ያስታወሱት ጠበቃው፤ ፍርድ ቤቱም ክስ የቀረበባቸው በመሆኑ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ማዘዙን ጠቅሰዋል።

በዚያ መነሻ መሰረት በትናንትናው ዕለት መስከረም 06/2013 ዓ.ም ከነበሩበት የፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በተለምዶ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወደ ሚባለው መዛወራቸውን ተናግረዋል።

አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ሌሎች ግለሰቦች ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መዛወራቸወን ጠበቃ ሔኖክ ሲያስረዱ፤ አቶ እስክንድር ከዚህ ቀደም ከስድስት ዓመታት በላይ በታሰሩበት ስፍራ እና ክፍል ዳግም መታሰራቸውን እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ አስክንድር ከሁለት ወራት በላይ ከቆዩበት ሌላ አስር ቤት ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከተዘዋወሩ በኋላ በተለምዶ ዋይት ሐውስ ወደ ሚባለው ክፍል እንዳስገቧቸው መናገራቸውን አስረድተዋል።

የእነ እስክንድር የዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ

በዛሬው [ሐሙስ] ዕለት አቶ እስክንድር ነጋን ጭምሮ በክስ መዝገቡ ላይ የሚገኙ 4 ሰዎች በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበው ክሳቸው እንደተነበበላቸው ጠበቃቸው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዛሬው ችሎት ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸውን ክስ ለማንበብ ቀጠሮ መያዙን አስታውሰው፤ ክሱም ለእነ አቶ እስክንድር ነጋ መነበቡን ይናገራሉ።

ክሱ ከተነበበና አስተያየት ከተሰማ በኋላ በጠበቆች በኩል የዋስትና ጥያቄ መቅረቡን ጠበቃ አክሊሉ ገልጸዋል።

"የቀረበባቸው ክስ ዋስትና የሚያስከለክላቸው አይደለም" የሚሉት አቶ ሔኖክ፤ ይህንንም በማንሳት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው መጠየቃቸውን ገልፀዋል።

አቃቤ ሕግ በበኩሉ የዋስትና መብት ሊከበርላቸው አይገባም በማለት መከራከሩን የሚገልፁት ጠበቃው፤ ያቀረበውም መከራከሪያ እነአቶ እስክንድር ቢፈቱ ለአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ትልቅ አደጋ ይፈጠራል የሚል ነው።

ከዚያህ በተጨማሪም በዋስ ከእስር ቤት ቢወጡ ሌላ ወንጀል ሊፈጽሙ ስለሚችሉ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን ሊጠብቅ አይገባም ሲል ዐቃቤ ሕግ መከራከሩን ገልፀዋል።

ጠበቆችም ሆኑ አቶ እስክንድር ይህንን የዐቃቤ ሕግ መከራከሪያ በመቃወም የተከራከሩ ሲሆን አቶ እስክንድር፤ ፓርቲያቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የተሻለ አማራጭ ያለው ፓርቲ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣዩ ምርጫ የእነርሱ መወዳደር ለአገሪቱ ዲሞክራሲ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ ምርጫው በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት እንዲኖረው የእርሳቸው በምርጫ መሳተፍ ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዐቃቤ ሕግ እርሳቸው ቢወጡ አገሪቱ ትበጠበጣለች የሚለውን በመቃወምም "እንደውም አገሪቱ ትረጋጋለች" ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።

አቶ ስንታየሁ ቸኮል በበኩላቸው "አቶ ታከለ ኡማን አስጨንቃችሁታል" መባላቸውን በመጥቀስ፤ ማስጨነቃቸው ተገቢ እንደነበር ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ ሁለት ተከሳሾችም የቀረበው ክስ ተገቢ አይደለም በማለት የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው መከራከራቸውን ጠበቃ ሔኖክ ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱም የሁለቱንም ወገን መከራከሪያ ከሰማ በኋላ ብይን ለመስጠት ለማክሰኞ መስከረም 12/2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ማለትም ጳጉሜ 5/2012 የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዚደንት በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ ዐቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር አዋጅን በመተላለፍና ክስ መመስረቱን ይታወሳል።

በአቶ እስክንድር ላይ የቀረቡት ክሶች ኃይልን በመጠቀም መንግሥትን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራን የሚጠቅሱ ናቸው።

በክስ መዝገቡ ላይ የተከሰሱት ሰባት ሰዎች ሲሆን አራቱ የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።