ኮሮናቫይረስ ፡ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚላጥ የጫማ ሶል የሰራው ወጣት

አብርሃም ዮሐንስ

የፎቶው ባለመብት, ABREHAM YOHANNES

የምስሉ መግለጫ,

አብርሃም ዮሐንስ

2012 ዓ.ም በጤናውም፣ በትምህርቱም፣ በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በማኅበራዊውም ዘርፍ በርካታ ክስተቶችን አስተናግዷል። ከእነዚህ ክስተቶች አንዱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዋነኛው ነው።

ወረርሽኙ እንዲህ ዓለምን አዳርሶ፤ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል ብሎ የገመተ አልነበረም።

እንደ ዘበት በቻይና ሁቤይ ግዛት ዉሃን ከተማ የጀመረውና በመጀመሪያ የከተማዋን ነዋሪዎች አስጨንቆ የነበረው የኮሮናቫይረስ፤ በአጭር ጊዜ አህጉራትን አዳርሶ የዓለም አገራትን በተመሳሳይ ስጋት ውስጥ ሲጥል ጊዜ አልፈጀበትም።

ይሄ ነው ታዲያ ሁሉም በየፊናው ወረርሽኙን የሚገታ አንዳች ነገር ለማግኘት መራወጥ የጀመረው። ፈጠራው የሰላምታ አሰጣጥን ከመለወጥ ነበር የጀመረው። አንዳንዱ በክናድ፣ አንዳንዱ በእግር፣ ሌሎች እጅ በመንሳት ንክኪን በማስወገድ በሽታውን ለመካላከል ሞክረዋል።

ይህ በሽታ ያልቀየረው ነገር የለም ማለት ይቻላል። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛንም 'ላይቀር ነገር' በሚል ወደ ፋሽንነት የለወጡትም ብዙዎች ናቸው። አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ፣ እጅን ለመታጠብ የተለያዩ መላዎች ተግባር ላይ ሲውሉም ተስተውለዋል።

ከእጅ ንክኪ ነፃ ከሆነ የእጅ ማስታጠቢያ እስከ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ ሮቦቶች ድረስ ተፈጥረዋል።

በኢትዮጵያም ባለፈው ዓመት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስምንት የፈጠራ ሥራዎች በአዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት መመዝገባቸውን በጽ/ቤቱ የፓተንት መርማሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ጣፋ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ለዛሬ አንዱን እናጋራችሁ።

'ፉትኤንዶ'

የፈጠራ ሥራውን ፉትኤንዶ የሚል ስያሜ ሰጥቶታል። በእንግሊዝኛው ፉት (እግር) እና በተለምዶ 'ኤርገንዶ' ከሚባል ከፕላስቲክ ከሚሰራ ነጠላ ጫማ ስያሜን አዳቅሎ ነው ስያሜውን የሰጠው (ፉት + ኤርገንዶ)። ፉትኤንዶ የሚላጥ የጫማ ሶል ነው።

የፈጠራ ሥራው ባለቤቱ አብርሃም ዮሐንስ ይባላል።

አብርሃም የ22 ዓመት ወጣት ሲሆን የሲቪል ምህንድስና የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ነው። የፋሽን ሞዴልም እንደሆነ ይናገራል። በዚሁ ዘርፍ ለአምስት ዓመታት ያህል ሰርቷል፤ ለሦስት ዓመታት ያህል ደግሞ ሞዴሊንግ አስተምሯል።

ይሁን እንጅ ይህ ወረርሽኝ ያልነካው የለምና የእርሱንም ሥራ አስተጓጉሎበታል።

ነገር ግን ከዚሁ በሽታ ጋር በተያያዘ የፈጠራ ሥራ ለማበርከት ምክንያት ሆኖታል።

የፎቶው ባለመብት, ABREHAM YOHANNES

የምስሉ መግለጫ,

የጫማው ሶል ንድፍ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሁሉም ሰው ትኩረቱ እጅን ከንክኪ ማቀብና ማፅዳት ላይ ቢሆንም፤ የትም አዙሮ በሚመልሰን ጫማ ወደ ቤትም ሆነ ወደ ቢሮ ይዘነው የምንገባው ቆሻሻ ግን አብርሃምን ያሳስበው ነበር።

አብርሃም እናቱ የስኳር ህመምተኛ በመሆናቸው እርሳቸው ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ከቤት ሲወጣ አንድ ትርፍ ጫማ ይዞ እንደሚወጣና ወደ ቤት ከመግባቱ በፊት ጫማውን እንደሚለውጥ አጫውቶናል።

በእርግጥ አብርሃምን ለፈጠራ ሥራው የገፋፋው ምክንያት ይህ ብቻ አይደለም። ወረርሽኙ በተከሰተ ሰሞን በጣሊያን እና ስፔን ውስጥ የሌሎችን ሕይወት ለማትረፍ ሲሉ የራሳቸውን ሕይወት ያጡ የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ ልቡን ስለነካውም ነው።

ከዚህ በኋላ ነበር ለእጃችን ጓንት፤ ለአፋችን ማስክ እንዳለ ሁሉ ለጫማችን ለምን ሽፋን አልሰራለትም ሲል ያሰበው። ይህ የፈጠራ ሥራው በተለይ ጫማን እንደልብ መቀየር በማይቻልባቸው ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና የመሳሰሉት ስፍራዎች ውስጥ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን እምነት አለው።

ይህ የጫማ ሶል ስለሚለጠጥ ለየትኛውም ዓይነት ጫማና የጫማ ቁጥር መሆን የሚችል ነው።

ሶሉ በየትኛውም ዓይነት መንገድ ላይ ቢራመዱበት የማይቀደድ ሲሆን የወዳደቁ ፕላስቲኮችን እንደገና በመጠቀም በቀላሉ መስራት የሚቻል ነው ይላል አብረሃም።

የፈጠራ ሥራውን ለማስመዝገብ ሲያስብም ወደ 27 ዓይነት የሴቶች ጫማ፣ ሸራ ጫማዎች፣ ስኒከሮች ላይ እንደሞከረው የሚናገረው አብርሃም፤ ለሁሉም ዓይነት ጫማ ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ መሰራቱን ይናገራል።

የፈጠራ ሥራው ወረርሽኙ ከተገታ በኋላም ንፅህናን ለመጠበቅ ስለሚረዳ አገልግሎቱ በዘላቂነት እንደሚቀጥል አብረሃም ያምናል።

ምንም እንኳን ሶሉን ለመለጠፍና ለመላጥ በእጅ መንካት ግድ ቢልም፤ አንዴ አጥልቆም ሆነ አውልቆ እጅን ማፅዳት ይቀላል ይላል።

"ይህ የፈጠራ ሥራ ለዓለም አቀፍም ገበያም ሊውል የሚችልበት እድል አለው" የሚለው አብርሃም፤ እስካሁን ግን የሚደግፈው እንዳላገኘ ይናገራል።

አብረሃም ይህንን የፈጠራ ሥራውን ከሐሳብ አንስቶ ወደ ተግባር ባመጣበት ሂደት ውስጥ 12 ሺህ ብር ገደማ እንዳወጣበት ገልጿል።

ይህንን የኮሮናቫይረስን መስፋፋት ለመከላከል በጫማ ሶል ላይ ተደርጎ ወደ ቤትም ሆነ ወደ የትኛውም ቦታ ሲገባ ሊላቀቅ የሚችለውን የፈጠራ ሥራውን አብረሃም በስፋት አምርቶ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ አለው።