የትግራይ ምርጫ ፡ "እኛ በሕዝብ ድምፅ እንጂ በችሮታ ምክር ቤት አንገባም" ሳልሳይ ወያነ

የትግራይ ክልላዊ ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ሕገወጥ ነው የተባለውና ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ አዲሱ ምክር ቤት ዛሬ ሥራውን ሲጀምር ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ ያለድምጽ እንዲሳተፉ የሚያስችል አዲስ አዋጅ አፀደቀ።

በዚህ መሰረት በምርጫው ከሚያዘው 190 የምክር ቤቱ መቀመጫ ውጪ በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያለድምጽ የሚሳተፉበት ተጨማሪ 15 ወንበሮች እንዲኖሩ ወስኗል።

የመቀመጫው ክፍፍልን በሚመለከት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በድምር ያገኙት 183 ሺህ ድምጽ ለ15 የምክር ቤቱ ወንበሮች ተከፋፍሏል።

በዚህ ስሌት መሰረትም ባይቶና ሰባት፣ ውናት አምስት፣ ሳልሳይ ወያነ ሁለት እንዲሁም አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አንድ መቀመጫ በምክር ቤቱ ውስጥ ያለድምጽ እንዲያገኙ ተወስኗል።

በትግራይ ክልል በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ህወሓት 189 ወንበር ሲያገኝ ባይቶና የቀረውን አንድ ወንበር ማግኘቱ የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ማሳወቁ ይታወሳል።

በዚህ የምርጫ ውጤት ድልድል አንድ ወንበር ብቻ ለባይቶና ፓርቲ እንዲሰጥ ቢወሰንም ባይቶና ግን ምክር ቤት ለመግባት ፍቃደኛ እንዳልሆነ ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

የፓርቲዎች ምላሽ

ይህንን ተከትሎም ሌሎች በምርጫው ድምጽ ያላገኙ አራት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በምክር ቤቱ ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ በሚመለከት በትናንትናው ውይይት ማካሄዳቸው ተነግሮ ነበር።

የትግራይ ምክር ቤትም አራቱን ተቀናቃኝ ፓርቲዎች በዝግ ስብሰባ በመጥራት "ድምጽ የማትሰጡበት ወንበር ብንሰጣችሁ ምን ይመስላችኋል?" የሚል ጥያቄ እንዳቀረበላቸው የትግራይ ነጻነት ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ግርማይ በርሄ ይናገራሉ።

በዚህ ሐሳብ ላይ አራቱ ፓርቲዎች ያንፀባረቁት አቋም የተለያየ ነው።

የሳልሳይ ወያነ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክንፈ ሐዱሽን "ምክር ቤት ትገባላችሁ ወይ?" ተብሎ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ "እኛ ምክር ቤት መግባት የምንፈልገው ሕዝብ መርጦን እንጂ በችሮታ አይደለም። ድምፅ በማንሰጥበት በእነሱ በኩል ስጦታ በሚመስል መልኩ የተወሰነን ወንበር አንቀበልም" ብለዋል።

አቶ ክንፈ ይህንን ሃሳብ ውድቅ ያደረጉበትንም ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶችም ያስረዳሉ።

"በተደረገው ምርጫ መሰረት መቶ በመቶ ህወሓት እንዳሸነፈ እየታወቀ ከዚያ ውጪ ያለ አሰራር ግን ሕጋዊ የሆነ መሰረት የለውም" ይላሉ።

"ቀድሞ የወጣውን የምርጫ ሕግ መሰረት ያላደረገ ሥራ እንዲሰራ አንፈልግም። ላለፈ ምርጫ ሕግ አሁን ማውጣት አያስፈልግም ምክንያቱም ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ ስለማይሰራ" በማለት አካሄዱ ሕጋዊ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል ምርጫ ከመደረጉ በፊትም የምርጫ ሥርዓቱን በተመለከተ 'ሚክስድ ፐሮፖርሽን' [ቅይጥ ተመጣጣኝ] ተብሎ የሚጠራው አሰራር በአዋጁ እንዲካተት ፓርቲያቸው ሐሳብ ቢያቀርብም ተቀባይነት እንዳላገኘ ይናገራሉ።

ይህ የውክልና ሥርዓት የአብላጫና ንፅፅራዊ (Majority and Proportional) የድምፅ አሰጣጥን የሚከተል ሥርዓት ነው።

"ድሮም እንዲህ አይነት ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ነበር፤ ይሄ የምርጫ ሥርዓት አዋጅ ሆኖ ቢወጣ ኖሮ አሁን የተፈጠረውን ችግር የሚፈታ ነበር። ነገር ግን እነሱ በጊዜው አልተቀበሉትም" ይላሉ።

አቶ ግርማይ በርሄ በበኩላቸው የትግራይ ምክር ቤት የሰጣቸውን እድል እንደ አንድ የመታገያ መድረክ እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል።

"ምክርቤትም ሀሳባችን የምንገልፅበት አንድ መድረክ ነው። ስለዚህ ሀሳባችን የምንገልፅበት መድረክ ባገኘን ቁጥር ለመጠቀም ዝግጁ ነን፤ ለዚያም ነው ገብተን መታገያ እናደርገዋለን ነው እያለን ያለነው።" ይላሉ።

ሆኖም ፓርቲያቸው የምርጫው ኮሚሽኑ ህግ ጥሰት ፈፅሟል ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ።

በምርጫ አዋጁ 80/20 'ሚክስድ ፓራራል' መሰረት ከፍተኛ ድምፅ ኣግኝቷል የተባለው ህወሓት 190 ወንበሮች መውሰድ ይገባው ነበር የሚሉት አቶ ግርማይ

"ኮሚሽኑ ግን የህግ ጥሰት በመፈፀም 189 ለህወሓት የተቀረችው አንዲት ወንበር ደግሞ ለባይቶና ሰጥቷል። ይህ ህጋዊ እንዳልሆነ እና በስሌቱ መሰረት አንዱ ወንበርም ለህወሓት እንደሚመለከት ገልፀናል" ይላሉ።

የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን በተመጣጣኝ ውክልናው የመቀመጫ ድልድል ሕግ መሠረት ህወሓት ካገኛቸው 152 የምክር ቤት መቀመጫዎች በተጨማሪ 38 ወንበሮች አጠቃላላይ ለተወዳደሩት ፐርቲዎች ባገኙት ድምፅ መሰረት ይከፋፈላሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ነገር ግን ተርፈው ከነበሩትና በተመጣጣኝ ውክልና እንደሚከፋፈሉ ከተገለፀው 38 የምክር ቤት መቀመጫዎች ህወሓት 37.35ቱን አግኝቷል፤ በአጠቃላይ ድምርም 189 ወንበሮችን ወስዷል።

በተመጣጣኝ ውክልናው ክፍፍል ቀመር መስረት ቀሪዋን 0.65 ወይም አንድ ወንበር ለባይቶና ቢሰጥም ባይቶናም ወንበሩ ለነሱ ስለማይመለከት እንደማይቀበሉት ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ መግለፃቸው ይታወሳል።

አቶ ግርማይ በርሄም ወንበሮቹን ለባይቶና እንዲሰጥ የተደረገበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነና መቶ በመቶ ህወሃት ነው መውሰድ ያለበት ይላሉ። "በቀረችው አንዲት ወንበርም ብዙ ድምፅ ያለው ህወሓት ስለሆነ ስለዚህ በህጉ መሰረት ህወሓት 190 ወንበሮች መውሰድ አለበት ብለን ጨርሰናል።" ይላሉ ።

ሆኖም ግን ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደምም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተውጣጥተው በምክርቤት በመግባት ሃሳባቸውን እንዲሰጡ የሚያደርግ አሰራር አለው የሚሉት አቶ ግርማይ ይህም ተሞክሮም በተለያዩ ሃገራትም ያለ ነው በማለት ፓርቲያቸው ድምጽ ባያገኝም ወደ ምክርቤቱ ለመግባት እንደወሰኑ ይናገራሉ።

የአሲምባ ፓርቲ በትግራይ ምክር ቤት ድምጽ አልባ ሆኖ የመግባቱን ነገር እንደተቀበለው የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ዶሪ አስገዶም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትግራይ ምክር ቤት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ለምን ሃሳብ አቀረበ የሚል ጥያቄ ለአቶ ክንፈ ሐዱሽ አቅርበን ነበር።

"የምርጫ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ከሕዝቡም ሆነ ከተለያዩ ወገኖች የተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ምክር ቤት መግባት ነበረባቸው የሚሉ፤ እንዲሁም መቶ ፐርሰንት ተቀባይነት የለውም የሚል የተቃውሞ ድምፅ መምጣቱን ተከትሎ ያንን ለማረጋጋት ነውም" የሚሉት አቶ ክንፈ "በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ቅቡልነት እንዲኖረው ለማድረግ የታሰበ ይመስለናል" በማለትም ያስረዳሉ።

ሆኖም "የገዢው ፓርቲ የሚያመጣቸው ሃሳቦች፣ ለገዢው ፓርቲ ብቻ የሚጠቅሙ ሃሳቦች ላይ መሳተፍ አንፈልግም፤ ሕዝባችንንም ሆነ ድርጅታችንን የሚጠቅም ሃሳብ ነው የምናስቀድመው" ይላሉ።

ፓርቲው የቀረበለትን ግብዣ አለመቀበሉ ህወሓትን ሊያስከፋ አይችልም ወይ፣ ውሳኔውን ስትወስኑስ ከገዢው ፓርቲ ሊመጣ የሚችል ቅሬታ አያሰጋችሁም ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ክንፈ።

ሁሉም ፓርቲዎች አንቀበልም የሚል ምላሽ እንዳልሰጡና ውሳኔያቸው በገዢው ፓርቲ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ በማየት አይደለም እንዳልሆነና "ለሚመጣውም ማንኛውም ሁኔታ ዝግጁ ንነ፤ ውሳኔያችን ከድርጅታችንና ከህዝባችን መርህና ጥቅም ጋር ይሄዳል ወይስ አይሄድም የሚል ነው" ብለዋል።