ሰሜን ኮሪያ አንድ የደቡብ ኮሪያን ባለስልጣንን 'ገድላ አቃጥላለች' ተባለ

ደቡብ ኮሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች አንድ የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣንን ተኩሰው ከደገሉ በኋላ ሬሳውን ማቃጠላቸውን የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ክስተቱንም ''እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር'' በማለት ገልጾታል።

ደቡቡ ኮሪያ እንደገለጸችው ባለስልጣኑ የአሰሳ ጀልባ ላይ ሳለ ነበር በድንገት የተሰወረው። ከቆይታ በኋላም አስክሬኑ በሰሜን ኮሪያ የውሃ ክልል ውስጥ መገኘቱ ተገልጿል።

''የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ተኩሰው ነው የገደሉት። በመቀጠል አስክሬኑ ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ በእሳት አቃጥለውታል'' ብሏል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ላይ።

ይህንን መረጃ ማግኘት የቻልኩትም የተለያዩ ወታደራዊ መረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን በመጠቀም ነው ሲል ገልጿል።

በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ምንም ያለው ነገር የለም።

ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያ ዜጋዬ ተገደለብኝ ስትል ይሄኛው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።