የአውስትራሊያው ባንክ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛውን ቅጣት ሊከፍል ነው

በሜልቦርን የሚገኘው የዌስት ፖክ ቅርንጫፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውስትራሊያው ዌስትፓክ ባንክ ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው የተባለውን 1.3 ቢሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር (1 ቢሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር) ሊከፍል እንደሆነ ተሰምቷል።

ባለፈው ዓመት የአውስትራሊያ የገንዘብ ነክ ወንጀሎች ተቆጣጣሪ እንዳስታወቀው ባንኩ እስከ 19 ሚሊየን የሚደርሱ ዓለማቀፍ የገንዘብ ዝውወሮችን በአግባቡ ማሳወቅ አልቻለም ።

እንደውም አንዳንድ በባንኩ በኩል የተደረጉ ክፍያዎች ከህጻናት ብዝበዛ ጋር የተያያዙ ናቸው ብለዋል ኃላፊዎች።

በአውስትራሊያ ሁለተኛ ትልቅ ባንክ የሆነው ዌስትፓክ ለተፈጠረው ነገር በሙሉ ይቅርታ ጠይቋል።

ባንኩ በአሜሪካ ዶላር ሲታሰብ በቢሊየኖች ዶላሮች መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን ፍርድ ቤት ውሳኔውን የሚያጸድቀው ከሆነ ደግሞ በአውስትራሊያ ታሪክ ከፍተኛው የቅጣት ክፍያ ይሆናል።

ነገር ግን ቅጣቱ ከዚህም በላይ ከፍ ያለ ሊሆን ይችል እንደነበር ተገልጿል። ምክንያቱም ሪፖርት ሳይደረጉ የቀሩት ዓለማቀፍ ዝውውሮች እስከ 23 ሚሊየን ሊደርሱ መቻላቸው ነው።

በእያንዳንዱ ዝውውር ደግሞ እስከ 21 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ድረስ ሊቀጣ ይችላል።

የዌስትፓክ ባንክ የቀድሞ ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ግለሰብ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባላፈው ዓመት ከስራቸው መልቀቃቸው የሚታወስ ነው።

የአሁኑ የባንኩ ስራ አስፈጻሚው ፒተር ኪንድ በበኩላቸው '' የተፈጠሩት ስህተቶችን ለማረምና ስህተቶቹ ከዚህ በኋላ ደግመመው እንዳይፈጸሙ ለማድረግ ቁርጠኞች ነን'' ብለዋል።

ባንኩ ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ የአውስትራሊያ የገንዘብ ነክ ወንጀሎች ተቆጣጣሪ ተቋም ያቀረበውን ክስ በፍርድቤት በኩል ለመጨረስ መስማማቱን አስታውቋል።

አብዛኛዎቹ የቀረቡበት ውንጀላዎች ባንኩ ዓለማቀፍ የገንዘብ ዝውውሮችን በአግባቡ ሪፖርት አለማድረግና የአውትራሊያን የገንዘብ ዝውውር ሕግ መጣስ የሚሉ ናቸው።

ከአውሮፓውያኑ 2013 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት በባንኩ ለመንግሥት ይፋ ሳይደረግ የቀረው የገንዘብ ዝውውር መጠን እስከ 11 ቢሊየን አውስትራሊያ ዶላር እንደሚደርስ ተቋሙ አስታውቋል።

አክሎም ባንኩ በሌሎች ሃገራት ላልተፈለገ ተግባር ሊውሉ የሚችሉ የገንዘብ ዝውውሮችን በአግባቡ ሳያጣራና ይፋ ሳያደርግ ቀርቷል ብሏል።

የዌስትፓክ ባንክ ተፎካካሪ የሆነው ኮመንዌልዝ ባንክም ቢሆን ከሁለት ዓመታት በፊት 53 ሺ የሚሆኑ ሪፖርት ካልተደረጉ ዝውውሮች ጋር በተያያዘ 700 ሚሊየን የአውስትራሊያ ዶላር መክፈሉ የሚታወስ ነው።