ኮሮናቫይረስ፡ ሳኡዲ አረቢያ የኡምራ ጉⶋን በመስከረም ወር መጨረሻ ልትጀምር ነው

ሙስሊም ሴት እየፀለየች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሰባት ወራት ያህል ተቋርጦ የነበረው የኡምራ ሃይማኖታዊ ጉዞ በዚህ ወር እንደሚጀመር ሳዑዲ አረቢያ አስታወቀች።

ከመስከረም 24፣ 2012 ዓ.ም ጀምሮም ስድስት ሺህ የሳዑዲ ዜጎች በየቀኑ የኡምራ ጉዞ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል።

ከሌላ አገር የሚመጡ የኡምራ ፀሎተኞችም ከጥቅምት 22፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ መምጣት ይችላሉ ተብሏል።

የየቀኑም ተጓዦች ቁጥር ወደ 20 ሺህ ያድጋል እንደሚያድገም ሳዑዲ አስታውቃለች።

ከእስልምና እምነት መሰረቶች አንዱ የሆነው የኡምራ ጉዞ በየትኛውም ወቅት ማከናወን ቢቻልም የሃጂ ጉዞ ግን የእስልምና እምነት ተከታዮች በህይወት ዘመናቸው አንዱ ሊያደርጉት የሚገባ የተቀደሰ ተግባር ነው።

በመላው ሙስሊም ማህበረሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሃጅ ጉዞ በዘንድሮው እክል ገጥሞታል። ከዚህ ቀደም ከሁለት ሚሊዮን በላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከየአገሩ ተሰባስበው ቢመጡም በዚህ አመት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሳዑዲ አረቢያ የፈቀደችው ጥቂት ሺዎች እንዲታደሙ ነው።

ከሃጅ ጉዞ በተለየ መልኩ በየዓመቱ የትኛውም ጊዜ ላይ መደረግ ለሚችለው ለኡምራ ጉዞ ቢያንስ በዓመት ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ወደ መካ ያቀኑ ነበር።

በየቀኑ 20 ሺህ ተጓዦችን ለመቀበል ያቀደችው ሳዑዲ አረቢያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል የሚለው በይፋ እስኪነገር የምትቀበለው ተጓዦች ቁጥር ተወስኖ እንደሚቆይም የሳኡዲ ዜና ወኪል የአገር ውስጥ ሚኒስትሩን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።

"ከሌላ አገራት የሚመጡ የኡምራ ፀሎተኞችና ተጓዦችን የምንቀበለው ቀስ በቀስ ሲሆን፤ ከወረርሽኙ ነፃ የሆኑ አገሮችንም ቅድሚያ እንሰጣለን" ማለታቸውም ተዘግቧል።

ተጓዦች የኮሮናቫይረስ ወርርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች እንደ የፊት ጭምብል፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅን ፅዳትን መጠበቅ እንደሚኖርባቸውም የዜና ወኪሉ አስነብቧል።

በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እስካሁን ባለው 330 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 4 ሺህ 452 ሰዎችም ህይወታቸው አልፏል።