የሰው ልጅ ምን ያህሉን የወርቅ ክምችት ተጠቅሞ ይሆን?

የወርቅ ክምችት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባሳለፍነው ወር እስከዛሬ ከነበሩት በሙሉ ከፍተኛው የተባለ የወርቅ ዋጋ ተመዝግቧል። 28.3 ግራም ወርቅ ከ2 ሺ ዶላር በላይ ሲሸጥ ነበር የከረመው።

ምንም እንኳን ወርቅ ዋጋ የሚወሰነው ከአቅርቦቱ እጥረት ጋር ባልተያያዘ መልኩ በወርቅ ሻጮች ቢሆንም ለመሆኑ በምድር ውስጥ ተከማችቶ የሚገኘው የወርቅ መጠን ምን ያክል ይሆን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ነው።

ወርቅ በዓለማችን እጅግ አዋጭ የሚባለው የኢንቨስትመንት አይነት ነው። በበርካታ የሰው ልጆች ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ቦታ ያለው ወርቅ አንዳንድ የኤሌክትሮኒክ እቃዎች ውስጥም ይገኛል።

ነገር ግን የሰው ልጅ የማያልቅ ሀብት አድርጎ የሚቆጥረው ወርቅ የሆነ ቀን ላይ አልቆ ማየታችን አይቀርም።

ባሳለፍነው የፈርንጆቹ ዓመት የሰው ልጅ እስከ 3531 ቶን ድረስ ከምድር ቆፍሮ ያወጣ ሲሆን በ2018 ከወጣው ወርቅ በአንድ በመቶ ያነሰ እንደሆነ የዓለም ወርቅ ካውንስል አስታውቋል።

ይህም ከ2008 በኋላ የወርቅ መጠን ቅናሽ ሲያሳይ የመጀመሪያው እንደሆን ካውንስሉ ገልጿል።

'' ምንም እንኳን የሰው ልጅ ወርቅ የማውጣት አቅሙ ከምንጊዜውም በበለጠ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም ከዚህ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን የወርቅ መጠን ቅናሽ እያሳየ መምጣት ሊጀምር ይችላል። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ አናገኝም ማለት አይደለም'' ብለዋል ዓለም ወርቅ ካውንስል ቃል አቀባይ የሆኑኡት ሃና ብራንድስታትር።

ስለዚህ ምን ያክል ወርቅ ቀርቶ ይሆን?

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በምድር ውስጥ ተከማችቶ የሚገኘውን ወርቅ መጠን ለመገመት ሁለት መንገዶችን መጠቀም ይቻላል።

የመጀመሪያው በአሁኑ ሰአት በምርምርና በፍለጋ የተገኘውና እየወጣ ያለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እስካሁን ድረስ ስለመኖሩ የሰው ልጅ ያማያውቀው የወርቅ ክምችት ነው።

ነገር ግን ስለመኖሩ የሰው ልጅ ያረጋገጠው ወርቅ መጠኑንም ጭምር ማወቅ የሚቻል ሲሆን እስካሁን ያልተገኘው ግን የትና ምን ያክል መጠን እንዳለው መገመት ከበድ ይላል።

በዚህም ስለመኖሩ የተረጋገጠ የወርቅ መጠን በአሁኑ ሰአት እስከ 50 ሺ ቶን ሊደርስ እንደሚችል የአሜሪካው ጂኦሎጂካ ሰርቬይ መረጃ ይጠቁማል።

እስካሁን ድረስም የሰው ልጅ 190 ሺ ቶን ወርቅ ከምድር ውስጥ ቆፍሮ አውጥቶ ለተለያዩ ተግባራት አውሎታል። ነገር ግን ይህ ቁጥር እርግጠኛ ሳይሆን ግምታዊ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው።

እነዚህን መረጃዎች ከግምት ውስጥ በማስገባትም የሰው ልጅ እስካሁን 20 በመቶ የሚሆነውን የወርቅ ክምችት እንደተጠቀመው መገመት ይቻላል። ነገር ግን በየዓመቱ የወርቅ ፍላጎት መጨመሩና ወርቅ የመፈለግና የማውጣት አቅም እየጨመሩ በመሆኑ በቅር ዓማታት ውስጥ እህ ቁጥር በእጅጉ ከፍ ሊል ይችላልእ።

በአሁኑ ሰአት የሰው ልጅ በባህላዊ መንገድ ወርቅ ፈልጎ ቆፍሮ ማውጣትን እየተወ ይገኛል። የወርቅ ክምችት ያለበትን ቦታ ለማወቅ በተትላይት ጭምር የታገዘ ፍለጋ የሚደረግ ሲሆን ወርቁን ከምድር ውስጥ ለማውጣትም ቢሆን ሮቦቶችን የሚጠቀሙ ድርጅቶች በርካታ ናቸው።

በዓለማችን ላይ እስካሁን ድረስ ከፍተኛው የሚባለው የወርቅ ክምችት የተገኘው በደቡብ አፍሪካ 'ዊትዋተርስራንድ' በሚባለው አካባቢ ሲሆን የዓለማችንን 30 በመቶ የወርቅ ምርትም አቅርቧል።

ሌላ ከፍተኛ ወርቅ የሚመረትባቸው አገራት መካከል ደግሞ እነ ቻይና፣ አውስትራሊያ፣ ኢንዶኔዢያ እና አሜሪካ ይጠቀሳሉ።

በአሁኑ ሰአት ቻይና የዓለማችን ቁጥር አንድ የወርቅ አምራች ስትሆን እንደ ካናዳ፣ ሩሲያ እና ፔሩም ቢሆኑ ከፍተኛ አምራች ከሚባሉት ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውን የዓለም ወርቅ ካውንስል መረጃ ይጠቁማል።

በድርጅት ደረጃ ደግሞ በአሜሪካ ኔቫዳ የሚገኘው 'ባሪክ ጎልድስ ማጆሪቲ' የተባለው ድርጀት በዓለማችን ትልቁ ወርቅ አምራች ሲሆን በዓመት እስከ 99 ሺ ኪሎግራም ወርቅ ያወጣል።

ምንም እንኳን የሰው ልጅ አዳዲስ የወርቅ ማውጫዎችን እየፈለገና እያገኘ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት ወርቅ በብዛት የሚመረትባቸው አከባቢዎች ቢያንስ ላለፉት አስር ዓመታት ወርቅ ሲወጣባቸው የነበሩ ናቸው።

የሰው ልጅ ከሚያወጣው ወርቅ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ከላይ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ብዙ ርቀት ወደውስጥ ተቆፍሮ ነው የሚገኘው።

''ወርቅ ፍለጋ ከዓመት ዓመት እየከበደ መጥቷል። እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉት አገራት ሰፋፊ አካባቢዎችን በማሰስ በቀላል ወጪና ጉልበት ይገኝ የነበረው ወርቅ በአሁኑ ሰአት በጣም ከባድ ሆኗል'' ይላሉ ቃል አቀባዩ።

''በሌላ በኩል ደግሞ የቻይና ወርቅ ማውጫዎች በጣም ትንንሽ ስለሆኑ በዘመናዊ መሳሪያ መታገዝ ግድ ይላቸዋል። በዚህም ወጪው ከዓመት ዓመት ከፍ እያለ መጥቷል'' በማለት አክለዋል።

ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምንም ያልተነካ የወርቅ ክምችት መኖሩ ለጊዜውም ቢሆን ተስፋ የሚሰጥ ነው። እንድ ምዕራብ አፍሪካ ባሉ አገራት ተስፋ ሰጪ የሆነ የወርቅ ክምች ታይቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ወርቅ የሚገኘው በምድራችን ብቻ አይደለም። ጨረቃ ላይ ጠቀም ያለ የወርቅ ክምችት እንዳለ ይነገራል። ነገር ግን ይህንን ወርቅ ቆፍሮ አውጥቶ ወደ ምድር ማጓጓዝ በራሱ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅና ኪሳራ ውስጥ ሊከት የሚችል ነው።

የዓለማችን ቀዝቃዛዋ አህጉር አንታርክቲካም ብትሆን በውስጧ ወርቅ እንደሚገኝ ተረጋግጧል። ነገር ግን ባለው ከባድ የአየር ጸባይ ሁኔታ ምክንያት አንዲት ግራም ወርቅ እንኳን ማውጣት የማይታሰብ ነው።