ኮሮናቫይረስ፡ አፍሪካ ቫይረሱን ለመቆጣጠር በወሰደችው እርምጃ ተመሰገነች

ጭምብል ያጠለቁ ኢትዮጵያውያን

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) ዋና ኃላፊ የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የወሰዱትን እርምጃ በማመስገን አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አፍሪካ እስካሁን ከ1.4 ሚሊዮን በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን ከ34 ሺ በላይ ደግሞ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ይህ ቁጥር ከአውሮፓ፣ እስያ እና አሜሪካ ከታየው የቫይረሱ ስርጭት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ነው

ቀደም ብለው የተጀመሩ የምርመራና የመከላከል ስራዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር እንደረዱ የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል ዋና ኃላፊ ጆን ኒኬንጋሶንግ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሲሰዲሲ 55 አባል አገራት ያሉት ማዕከል ነው።

አፍሪካ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዜጎች ያሏት ቢሆንም በዓለም ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሲሰላ ግን አፍሪካ ድርሻዋ 5 በመቶ ብቻ ነው። በመላው ዓለም በቫይረሱ ከሞቱት ሰዎች መካከል ደግሞ ደግሞ አፍሪካ 3.6 በመቶ ብቻ ነው ድርሻዋ።

ዋና ኃላፊው እንደሚሉት ምንም እንኳን በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም አገራት በትክክል መረጃዎችን አለመስጠታቸው በወቅቱ አሳሳቢ ነበር።

'' ምናልባት በየቦታው የተከሰተውን የወረርሽኙን ስርጭት እንደሌላ የዓለማችን ክፍል አልተከታተልነው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ቀደም ብሎ ሲባል እንደነበረውና እንደተፈራው በአፍሪካ በርካታ ሰዎች በየመንገዱ ሞተው አልተመለከትንም'' ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት የመጀመሪያው የቫይረሱ ኬዝ ሪፖርት ከተደረገበት ቀን አንስቶ የተለያዩ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ሲወስዱ ነበርም ተብሏል። እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ በርካታ አገራት ጠበቅ ያለ አገር አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ ሲጥሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ደግሞ ቀለል ያሉ ገደቦችን በመጣል በሌላ ጎን የምርመራ አቅማቸውን ከፍ በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ነበር።

ዋና ኃላፊው አክለውም የአፍሪካ አገራት የቫይረሱን ስርጭት ከመቆጣጠር አንጻር ያሳዩት መተባበርና "ወንድማማቻዊ ስሜት" የሚደነቅ ነው ብለዋል።

''በተጨማሪም በበርካታ አገራት፤ እኔ የምኖርባት አዲስ አበባን ጨምሮ ሰዎች በየመንገዱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው ሲንቀሳቀሱ ተመልክቻለው። በአዲስ አበባ 100 በመቶ ማስክ ይደረግ ነበር''

አፍሪካ ከአጠቃላይ ህዝቧ መካካል አብዛኛው በአማካይ ወጣት መሆኑ ደግሞ ለቫይረሱ ዝቅተኛ ስርጭት አስተዋኦ እንዳለውም ዋና ኃላፊው ጨምረው አስረድተዋል።

እነዚህ ነገሮች በሙሉ እንዳሉ ሆነው እንደ ኢቦላ አይነት ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች ምክንያት በአፍሪካ ከዚህ በፊት ልምድ ስለነበረ በኮሮረናቫይረስ የተያዙትን መለየትና ንክኪ ያላቸውን አድኖ ማግኘት ላይ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል'' በማለት የአፍሪካን ስኬት ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰአት በኮቪድ-19 ከሚያዙና ከተያዙ ሰዎች ውስጥ ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛውን ቁጥር የምትይዝ ሲሆን በአጠቃላይ ካለው ቁጥር ለግማሽ የቀረበው የተመዘገበውም በዚችው አገር ነው።

ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ ቁጥሩ እንዲህ ከፍ ሊል የቻለው አገሪቱ በየቀኑ የምትመረምረው ሰው ብዛት በጣም ብዙ ስለሆነ ነው።

እስካሁን ባለው መረጃ ደቡብ አፍሪካ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የመረመረች ሲሆን በአጠቃላይ 50 የሚሆኑ የአፍሪካ አገራት በጋራ ያደረጉት ምርመራ ግን በቅርቡ ነው ከ10 ሚሊየን የተሻገረው።

''በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መሰረት በአፍሪካ ያለው ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም በበቂ ሁኔታ ምርመራ እየተደረገ አለመሆኑ ለዚህ በምክንያትነት ይቀርባል። በዚህም ምክንያት የአፍሪካ ስኬት በአግባቡ እየታየ አይደለም''