የቤላሩስ ምርጫ፡ የአውሮፓ ሕብረት የቤላሩስን ፕሬዝዳንት አልቀበላቸውም አለ

የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ

የአውሮፓ ህብረት የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮን እንደ ፕሬዝዳንትነት እንደማይቀበላቸው አስታውቋል። አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ከቀናት በፊት ነበር በሚስጥር በካሄደ ስነስርአት ለስድስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት የሆኑት።

የሕብረቱ የዲፕሎማሲ ኃላፊ "በሚስጥር የተደረገው ስነስርአትና በአጨቃቃጪ ሁኔታ ፕሬዝዳንቱ መመረጣቸው ፕሬዝዳንቱ ምንም አይነት ዴሞክራሲያዊ ተቀባይነት እንደሌላቸው ያሳያል" ብለዋል።

የቤላሩስ ተቀናቃኝ ፓርቲም ምርጫው ፕሬዝዳንቱ እንዲያሸንፉ በሚያስችል መልኩ ተጭበርብሯል ብሎ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ለስድሰተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ተደርገው መመረጣቸውን ተከትሎ በቤላሩስ ከፍተኛ ተቃውሞ እየተካሄደ ሲሆን በዋና ከተማዋ ሚንስክ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው እየተዘገበ ነው።

የአገሪቱ ምርጫ ከሚሽን እንዳለው ለ26 ዓመታት በስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ 80 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል። ይህን ተከትሎም በቤላሩስ ለሳምንታት የቆየ ተቃውሞ እየተደረገ ነው።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ የፕሬዝዳንቱን በአለ ሲመት የታደሙ ሲሆን ስነስርአቱም የተካሄደው ሚንስክ ውስጥ በሚገኘው በብሄራዊ ቤተመንግስት ነው። በወቅቱ በርካታ መንገዶች ዝግ እንዲሆኑ ተደርገው ነበር።

ስነስርአቱን የታደሙት አብዛኛዎቹ እንግዶችም ታማኝ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች ናቸው።

አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ደግሞ ስነስርአቱን 'የሌባዎች ስብሰባ' በማለት ገልጸውታል።

'' የአውሮፓ ሕብረት ተጠናቅሮ የቀረበውን የሀሰት የምርጫ ውጤት አይቀበለውም። ይህንን መሰረት በማድረግ በቅርቡ የተካሄደው በአለ ሲመትና ፕሬዝዳንቱ አሸንፌያለሁ የሚሉበት መንገድ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምንም ተቀባይነትና መሰረት የለውም'' ብለዋል የሕብረቱ የዲፕሎማሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል።

'' ይህ በአለ ሲመት የበርካታ ቤላሩሳውያንን ፍላጎት በቀጥታ የሚጻረር ነው። ህዝቡም ተቃውሞውን አደባባይ በመውጣት ገልጿል፤ ይህ ደግሞ አገሪቱን ወደበለጠ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ሊከታት ይችላል'' ብለዋል ኃላፊው።

አክለውም የአውሮፓ ሕብረት ከዚህ በኋላ ከቤላሩስ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በድጋሚ እንደሚያየው ገልጸዋል።