የአሜሪካ ምርጫ፡ ትራምፕ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን አልቀበልም አሉ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ምርጫ ከተሸነፉ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን እንደማይቀበሉ ተናገሩ።

ፕሬዘዳንቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የሚሆነውን እናያለን እስኪ” ብለዋል።

የመራጮች ድምጽ በፖስታ ተልኮ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው እና ውጤቱ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊያመራ እንደሚችል ገልጸዋል።

ብዙ ግዛቶች መራጮች ለኮሮናቫይረስ እንዳይጋለጡ ድምጻቸውን በፖስታ እንዲልኩ እያበረታቱ ነው።

ትራምፕ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ካሉ ምን እንደሚከሰት በግልጽ አልታወቀም።

ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን እንደሚሉት፤ ትራምፕ ውጤቱን አልቀበልም ካሉ የአገሪቱ መከላከያ ከዋይት ሀውስ ያስወጣቸዋል።

ትራምፕ ምን አሉ?

ባይደን ትራምፕን ካሸነፏቸው ትራምፕ ሥልጣን በሰላም ያስረክቡ እንደሆነ በጋዜጠኛ ተጠይቀው ነበር። እሳቸውም በፖስታ ድምጽ የመስጠት ሂደት ላይ እንደማይተማመኑ ተናግረዋል።

እአአ በ2016 ትራምፕ በሂላሪ ክሊንተን ከተሸነፉ ውጤቱን እንደማይቀበሉ መግለጻቸው አይዘነጋም።

ትራምፕን አልፎ አልፎ የሚተቹት ሪፐብሊካኑ ሚት ሮምኒ “ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የዴሞክራሲ መሠረት ነው። አለበለዚያ እንደ ቤላሩስ እንሆናለን። ሕገ መንግሥቱን የማይቀበል ፕሬዘዳንት ተቀባይነት አይኖረውም” ሲሉ ትዊት አድርገዋል።

ዴሞክራቶች ምን አሉ?

ባይደን የትራምፕ ንግግር “ምክንያት አልባ ነው” ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ሊሰነዝሯቸው የሚችሉ ማንኛውንም ማጭበርበሪያ መንገዶች ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውም አክለዋል።

ዴሞክራቶች “አሜሪካ መርህ የሚጥሱን ከዋይት ሀውስ በሰላም ማስወገድ ትችላለች” ሲሉም የባይደንን ሐሳብ አጠናክረዋል።

ወግ አጥባቂዎች ባይደንን በአገሪቱ ጠብ በማጫር ይከሳሉ።

የቀድሞዋ የትራምፕ ተፎካካሪ ሂላሪ ክሊንተን “በማንኛውም ሁኔታ እጅ መስጠት የለብህም” በማለት ለባይደን መልዕክት አስተላልፈዋል።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳይ

ሪፐብሊካኖች እና ዴሞክራቶች ከምርጫው በፊት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ይመረጥ አይመረጥ በሚለውም እየተወዛገቡ ነው።

ትራምፕ የምርጫው ውጤት ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ማምራቱ እንደማይቀርና ከምርጫው በፊት ዳኛ መሰየም እንዳለበት ተናግረዋል።

ዴሞክራቶች “ያጭበረብራሉ። ስለዚህ ይህ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ፊት መከናወን አለበት” ሲሉም ትራምፕ ተደምጠዋል።

ባለፈው አርብ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዮት ሩት ቤደር ጊንስበርግ ምትክ ሌላ ሴት እጩ እንደሚያቀርቡም ፕሬዝዳንቱ ይፋ አድርገዋል።

እጩዋ በምክር ቤት ይሁንታ ካገኙ የወግ አጥባቂ ዳኞችን ቁጥር 6 ለ 3 ያደርገዋል ብለው የትራምፕ ደጋፊዎች ተስፋ ያደርጋሉ።

ዳኛ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አባልነት ከተመረጠ ወይም ከተመረጠች እስከ እድሜ ልክ ያገለግላል ወይም ታገለግላለች።

በፖስታ የሚላክ ድምጽ ሊጭበረበር ይችላል?

የምርጫ ኮሚሽነር ኤለን ዌይንትራብ በፖስታ የሚላክ ድምጽ ይጭበረበራል መባሉ “መሠረተ ቢስ ነው” ይላሉ።

በእርግጥ በፖስታ ድምጽ ተልኮ የተጭበረበረባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

ለምሳሌ ዘንድሮ ኒው ጀርሲ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ በፖስታ የተላኩ ድምጾች መገኘታቸውን ተከትሎ ሁለት የዴሞክራት ካውንስለሮች ምርጫ በማጭበርበር ተከሰዋል።

ሆኖም ግን በአሜሪካ የፖስታ ምርጫ ሊጭበረበር የሚችልበት እድል ከ0.00004% እስከ 0.0009%

መሆኑን 2017 ላይ የተሠራ ጥናት ይጠቁማል።

በፖስታ የሚላክ ድምጽ ሊጠፋ ይችላል። ኤምአይቲ የሚሠሩት የፖለቲካ ሳይንቲስት እንደሚሉት 2008 ላይ በተካሄደ ምርጫ በፖስታ ከተላከ ድምጽ የጠፋው ከአምስት አንድ ነው። ይህም 7.6 ሚሊዮን ድምጽ ማለት ነው።