የሴቶች መብት፡ በፈረንሳይ አንድ ሴት ‘ቀሚስ በመልበሷ’ መተንኮሷ ቁጣ ቀሰቀሰ

ቀሚስ የለበሰች ሴት

የፎቶው ባለመብት, AFP

ፈረንሳይ ውስጥ አንዲት ሴት ‘ቀሚስ በመልበሷ’ መተንኮሷን ተከትሎ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ ነው።

ኤልሳቤጥ የተባለችው የ22 ዓመት ተማሪ “ቀሚስ በመልበሴ ሦስት ግለሰቦች በቡጢ መተውኛል” ብላለች።

የፈረንሳይ መንግሥት ድርጊቱን ተቀባይነት የሌለው በማለት ኮንኖታል።

ከሁለት ዓመት በፊት ጎዳና ላይ የሚደርስ ትንኮሳን የተመለከተ ሕግ ከወጣ ወዲህ 1800 ቅጣት ተላልፏል።

ኤልሳቤጥ ወደ ቤቷ እየሄደች ሳለ ነበር የተተነኮሰችው። ከሦስቱ ወንዶች አንዱ “ያቺን ቀሚስ ያደረገችውን እዩ” ማለቱን ተናግራለች።

ከዛም ሁለቱ ወንዶች ይዘዋት ሦስተኛው ግለሰብ ፊቷን መቷታል። አይኗም በልዟል።

ግለሰቦቹ ከአካባቢው እንደተሰወሩ ኤልሳቤጥ ለፖሊስ ተናግራለች። ብዙ ሰዎች ስትደበደብ ቢያዩም አንዳቸውም ጣልቃ እንዳልገቡም ገልጻለች።

በዚህ ሳምንት የአገር ውስጥ ሚንስትር ዲኤታ ማርሊን ሺያፓ በሕዝብ መሰብሰቢያዎች ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስወገድ በምሥራቅ ፈረንሳይ ውይይት አካሂደው ነበር።

“ለጥቃቱ ተጠያቂው ሴቶች ወይም ቀሚሳቸው አይደለም” ብለዋል።

“ማንም ሴት ጥቃት የሚደርስባት ቀሚስ በመልበሷ ሳይሆን ጾተኛና ነውጠኛ ሰዎች ስላሉ ነው። እነዚህ ሰዎች ሕጉ በነሱ ላይ የሚሠራ አይመስላቸውም” ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም፤ ምን ለብሼ ልውጣ? ብለው ተማሪዎች እንዲያስቡ ማድረግ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጫና እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች ሴቶች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ፖሊሶች እርምጃ እንዲወስዱም አሳስበዋል።

ባለፈው ሐሙስ ሁለት ሴቶች ሙልሀውስ በተባለ ግዛት ሲጓዙ አንድ ግለሰብ ‘ቀሚስሽ አጠረ’ በሚል ጥቃት አድርሶባቸው ነበር።