ኮሮናቫይረስ ፡ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የምንወስዳቸውን ጥንቃቄዎችን በአንድ ጊዜ የሚከውነው መሳሪያ

ተክለወልድ ከፈጠራ ሥራው ጋር
የምስሉ መግለጫ,

ተክለወልድ ከፈጠራ ሥራው ጋር

ባሳለፍነው ዓመት በዓለማችን ካጋጠሙ ክስተቶች አንዱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው። ወረርሽኙ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖዎችን አሳድሯል።

ወረርሽኙ ስርጭቱን እያሰፋ ባቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። በተለይ በሽታው በመጀመሪያ ላይ ተከስቶ በነበረባቸው አገራት ውስጥ ዳግም እያገረሸ መሆኑ እየተነገረ ነው።

ቢሆንም ግን የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ያሉትን የመከላከያ ዘዴዎች በአግባቡ ተግባር ላይ ማዋል ከተቻለ የወረርሽኙን የመዛመት ፍጥነት መግታት እንደሚቻል ባለሙያዎች ይመክራሉ።

እነዚህን የቫይረሱን የመተላለፊያ መንገዶች የሚቀንሱ ዘዴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ፈጠራ የታከለባቸው አማራጮች እየቀረቡ ነው።

በኢትዮጵያም ባለፈው 2012 ዓ.ም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስምንት የፈጠራ ሥራዎች በአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት መመዝገባቸውን የተቋሙ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታቸው ጣፋ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት በጫማ ሶል ላይ የሚለጠፍና አስፈላጊ ሲሆን ተልጦ የሚወገድ ሽፋንን አስተዋውቀናችሁ ነበር። የዛሬው ደግሞ ልብሳችን ሳይረጥብ በጸረ ተህዋስ ለማጽዳት የሚያስችል የኢትዮጵያዊ ፈጠራን አቅርበናል።

ይህ የፈጠራ ሥራ የበርካቶችን ጭንቀት የሚያቃልል ይመስላል። ምክንያቱም መሳሪያው የተሰራው በአንድ ጊዜ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን ነው።

የጫማን ሶል ያፀዳል፣ ልብስን ሳያረጥብ በፀረ ተህዋስ ኬሚካል ያጥባል፤ ሙቀት ይለካል፤ የጤና መታወክ ገጥሞዎት ከሆነ ደግሞ ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ በጽሁፍና በድምፅ ትዕዛዝ ይሰጣል።

ይህ ብቻም አይደለም። የሚጠበቀውን ሂደት ሳይከተሉ ድንገት ዘው ብዬ እገባለሁ ካሉም መንገድዎን እንዳያልፉ በዘንግ ይዘጋብዎታል።

የሰውነት ሙቀትዎም ከጤናማ ሰው በላይ ሆኖ ልግባ ካሉም የሚገጥምዎት ተማሳሳይ ነው። እንዴት? ካሉ የፈጠራ ሥራው ባለቤት ተክለወልድ ወልደየሱስ ይህ ፈጠራ መሳሪያ እንዴት እንደሚሰራ ለቢቢሲ አብራርቷል።

እርሱ እንደሚለው ማሽኑ ዲጂታላይዝድ ነው። ከተገለፀው በላይም በማራቀቅ የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል።

የዚህ ማሽን ዋነኛ ሚናው ኮቪድ-19 በንክኪ የሚተላለፍ በመሆኑ በርካታ ነገሮችን ከሰው ንክኪ ነፃ ማድረግ ነው። ከዚህ ባሻገርም በማንኛውም ጊዜ ቤትንም ሆነ መሥሪያ ቤትን ከየትኛውም አይነት ባክቴሪያና ቫይረስ ነፃ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ ነው።

ማሽኑ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ከሆኑት መካከል የሰውነት ሙቀትን ይለካል። ከንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ ማፅጃ አለው። ሙሉ ልብስን ሳያረጥብ በጸረ ተህዋስ ያፀዳል። በተጨማሪም የተለያዩ ስፍራዎችን የረገጥንበትን ጫማችንንና የጫማንን ሶል በቆሙበት ስፍራ ላይ ያፀዳል።

በዚህ ሂደት ውስጥም በማሽኑ ውስጥ የሚያልፍ ሰው የሰውነት ሙቀቱ ከጤናማው መጠን የበለጠ ከሆነ፤ ማሽኑ ላይ በተገጠመው ፕሮግራም አማካይነት ግለሰቡ እንዳያልፍ ያደርገዋል። በተጨማሪም የሰውነቱ መቀት የወረርሽኙ ምልክት ሊሆን እንደሚችል በማመልከት ወደ ጤና ተቋም እንዲሄድ ምክር ይሰጣል።

ማሽኑ መልዕክትና ምክርን መስጠት የሚጀምረው ለማለፍ ሲሞክሩ ሳይሆን ከዚያ በፊት "እባክዎትን እጅዎትን ያፅዱ" በማለት በተገጠመለት ስክሪን ላይ በሚያሳየው ጽሁፍና በድምፅ አማካይነት ነው።

ይህ ከማሽኑ የሚተላለፈው መልዕክት ለአሁን በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዘጋጀቱን የሚገልጸው የፈጠራው ባለቤት ተክለወልድ፤ በአገር ውስጥ ቋንቋዎችም እንዲሰራ ለማድረግ ሃሳብ እንዳለውም ለቢቢሲ ተናገሯል።

ይህ የፈጠራ ሥራ ውጤት በማንኛውም የመኖሪያም ሆነ የመሥሪያ ቤት መግቢያ በሮች ላይ በቀላሉ የሚገጠምና አገልግሎት ለመስጠት የሚችል ነው።

ለዚህም ሲባል ይህንን የፈጠራ ሥራ በተለያየ መጠን ማዘጋጀት እንደሚቻል የሚናገረው ተክለወልድ፤ አሁን ላይ የሰራው 2 ሜትር ከ20 ሴንቲ ሜትር ቁመትና 1 ሜትር ስፋት እንዳለው ይናገራል።

በዚሁ ማሽን በኩል የሚያልፉ ተሽከርካሪዎችና ሰዎችን አቋቋም እና አጠቃላይ መጠናቸውንም የሚለይ ነው። በመሆኑም የፀረ ተህዋስ ኬሚካሉን ሲረጭ በሰዎችም ሆነ በተሽከርካሪዎች ቁመትና መጠን ልክ ይሆናል ማለት ነው።

ልብስ ሳይረጥብ እንዴት በፀረ ተህዋስ ኬሚካል ይፀዳል?

በአብዛኛው የምናውቃቸው ፀረ ተህዋስ ኬሚካሎች ፈሳሽ ወይም እርጥበት ያላቸው ናቸው። የተክለወልድ ፈጠራ ግን ከዚህ የተለየ ነው። የፈጠራ ሥራው ፀረ ተህዋስ ኬሚካል በመርጨት ልብስን ሳያረጥብ ከተህዋስ ያፀዳል።

ይህንን ለማድረግ ሁለት ዓይነት መንገዶችን ይጠቀማል። አንደኛው ከፍተኛ ሙቀት ሲሆን፤ ሙቀቱ ኬሚካሉ ልብሱን ሳያረጥብ እንዲበተን ያደርገዋል። በመሆኑም ልብሱ ላይ የሚያርፈው የተወሰነ መጠን ብቻ ይሆናል። ይህም ልብስን የሚያረጥብ አይደለም።

ሌላኛው መንገድ ደግሞ አውቶማይዜሽን [ፈሳሽን ወይም ጠጣር ነገሮችን ወደ አነስተኛ ቅንጣጢት የመቀየር ሂደት] ይባላል። ይህም 'አልትራሶኒክ አውቶማይዘር' የሚባል መሳሪያ በመጠቀም የሚከናወን ነው። ይህ መሳሪያ ፀረ ተህዋስ ኬሚካሉን ወደ ጭጋግነት በመለወጥ ነው የማፅዳት ሥራውን የሚያከናውነው።

ጫማን ለማጽዳትም ጫማዎትን ማውለቅ አሊያም ማገላበጥን አይጠይቅም። ልክ አንደ መኪና እጥበት እዚያው በቆሙበት ቦታ ላይ ነው ሁሉም ነገር የሚጠናቀቀው።

በመሳሪያው ላይ የተገጠመው የመቆሚያ ምልክት ቀዳዳዎች ያሉት ሲሆን በቦታው ላይ ሰው ሲቆም፤ የጫማውን ቅርፅ በመለየት ከሥር የፀረ ተሕዋስ ኬሚካሉን መርጨት በዚህ ሁኔታ ጽዳቱን ያከናውናል።

የፈጠራ ሥራው መነሻ

ተክለወልድ መላውን ዓለም ዕኩል እያስጨነቀ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በርካቶችን መቅጠፉና ብዙ ዘርፎችን ማናጋቱ ለፈጠራ ሥራው የተነሳበት ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ይናገራል።

ይህ ብቻ ግን አይደለም።

"ቫይረሱ አንዴ ብረት ላይ ይህን ያህል ሰዓት ይቆያል፣ ፕላስቲክ ላይም እንዲሁ፣ አየርም ላይ እየተባለ መተላለፊያ መንገዶቹ በውል ያልታወቁ በመሆኑ፤ ወደ ቤትና ወደ ቢሮ ስገባ እሳቀቅ ነበር" ይላል ተክለወልድ።

እጅ ምን ቢፀዳ በያዝናቸው ቁሳቁሶች አሊያም በልብስ ቫይረሱ ሊከተለን ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም ይናገራል።

በመሆኑም ይህን የፈጠራ ሥራ እውን ያደረገበት ምክንያት፤ ማሽኑ እጅንም፣ እግርንም፣ ልብስንም ስለሚያፀዳ፤ ሙቀትም ስለሚለካ ያለውን ስጋት በአንድ ቦታ ላይ ለመቀነስና የመተማመን ስሜትን ለመፍጠር ነው ብሏል።

በተጨማሪም ከስጋት የተነሳ "ወደ ሥራ ቦታ ለመሄድ ያለውን መሳቀቅም ይቀንሳል" ብሏል።

የፈጠራ ሥራውን ለመስራት የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች አገር ውስጥ በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ ከውጭ አገር ተፃፅፎ ለማስመጣት እንዲሁም የማሽኑን ፕሮግራሞች ለመስራት ብሎም ለመሞከር ሁለት ወር ገደማ እንደወሰደበት ይናገራል።

በገንዘብ ደረጃ ስንት እንዳስወጣው በውል አለማስላቱን የሚገልጸው ተክለወልድ፤ እስካሁን ባለው ወደ 50 ሺህ ብር ገደማ እንዳወጣበት ይገምታል።

የኮሮናቫይረስን በመከላከል በኩል ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ለሚሰጠው ለዚህ ማሽን የሚያስፈልገውን ሶፍትዌር እራሱ ያዘጋጀው ሲሆን ጓደኞቹ ደግሞ በቴክኒካዊ ጉዳዮች እንደረዱትም ይናገራል።

ተክለወልድ የፈጠራ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ካጠናቀቀ በኋላ ለመንግሥት ኃላፊዎችና ሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት የማሳየት እቅድ አለው።