እርጉዟን ሴት እየረጋገጠ የደበደባት አውስትራሊያዊ ተፈረደበት

የሲድኒ ፍርድ ቤት ሰውየው ድርጊቱን በ"ሙስሊም ጠልነት" የፈጸመው እንደሆነ ደርሶበታል

የፎቶው ባለመብት, NSW POLICE

የዛሬ ዓመት ግድም ኅዳር ወር በአውስትራሊያ ሲድኒ፣ በአንድ ሬስቶራንት በረንዳ ላይ እርጉዝ ሴትን ደብድቦ የዓለም መነጋገርያ የነበረው ነጭ አክራሪ ተፈረደበት።

የ44 ዓመቱ ስቲፕ ሎዚና፣ ወ/ሮ ራና ኢላዝማር ተባለች የ32 ዓመት እርጉዝ ሴትን ነበር አስተኝቶ የረጋገጣት።

ወ/ሮ ራና ኢላዝማር ያን የዘጠኝ ወር እርጉዝ ሳለች ነበረ፤ ከጓደኞቿ ጋር ካፌ ቁጭ ብላ ሻይ ቡና በማለት ላይ ሳለች ያልተጠበቀ ነገር የደረሰባት።

ይህ ሰው ድንገት ወደርሷ ተጠግቶ ገንዘብ እንድትሰጠው የጠየቃት ሲሆን ወዲያውኑ ባልተጠበቀ ሁኔታ አካላዊ ጥቃት ሰንዝሮባታል።

ክስተቱን የሚያሳየው ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጋራ በኋላ በአውስትራሊያ ብቻም ሳይሆን በመላው ዓለም ትልቅ መነጋገርያ ለመሆን በቅቶ ነበር።

ጉዳዩን የተመለከተው የሲድኒ ፍርድ ቤት ሰውየው ድርጊቱን በ"ሙስሊም ጠልነት" የፈጸመው እንደሆነ ደርሶበታል፤ ግለሰቡ ድብደባውን ሲፈጽምም "እናንተ እስላሞች…" እያለ ይናገር ነበር ብሏል ዐቃቤ ሕግ።

ሰውየው ነፍሰጡሯን ሴት 14 ጊዜ በቡጢ ከነረታት በኋላ በእግሩ ጭንቅላቷን መቷታል። በመጨረሻ የካፌው ተስተናጋጆች ተጋግዘው እርጉዟን ሴት ታድገዋታል።

ክስተቱን የሚያሳየው የደኅንነት ቪዲዮ በአውስራሊያ ሚዲያዎች ከታየ በኋላ በርካታ ሰዎች ቁጣቸውን ገልጸዋል። የሴቶች ጥቃት ይብቃ የሚሉ እንቅስቃሴዎችም እንዲቀሰቀሱ ምክንያት ሆኗል።

ወ/ሮ ኤላዝማር ለፍርድ ቤት ጥቃቱ የደረሰባት ሙስሊም በመሆኗ እንደሆነ ተናግራለች። ሙስሊም ጠልነትና የሴቶች ጥቃት እንዲቆም ጠይቃለች።

ዳኛው ክርስቶፈር ክሬግ ሰውየው ጤናው የተቃወሰ እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ ጥቃቱ በእሷም ሆነ በሚወለደው ልጅ ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያደርስ ይችል እንደነበር አብራርተዋል።

ወ/ሮ ኤላዝማር "መልካም ሰዎች ባያስጥሉኝ ኖሮ ሞቼ ነበር" ብላለች። ከጥቃቱ የታደጓትን ሰዎችም አመስግናለች።

ሆኖም ግን ለፍርድ ቤት እንዳብራራችው ከዚያ ጥቃት በኋላ ደጅ የመውጣት ፍርሃት እንዳደረባትና የደረሰባትን ጥቃት ለተመለቱት አራት ህጻን ልጆቿ ስለ ጉዳዩ ማብራራት ከባድ እንደሆነባት በመግለጽ የሥነ ልቦና ጫናውን አብራርታለች።

ጥቃት ፈጻሚው በበኩሉ ጠበቃ አልፈልግም ብሎ ራሱ ፍርድ ቤት የተከራከረ ሲሆን ብዙም ስሜት የማይሰጡ ነገሮችን በፍርድ ቤት ይናገር ነበር ሲሉ የአውስራሊያ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ዳኛው ፍርድ ሲሰጡ ሰውየው ከዚህ ቀደም ስኪዞፎርኒያ የተባለ የአእምሮ ህመም ተጠቂ እንደሆነ ተናግረዋል።

ወንጀለኛው በ2022 ዓ.ም በኋላ በምሕረት ከእስር ቤት ለውጣት ማመልከት ይችላል።