የአማዞን ኩባንያ ሮቦቶች ለሰራተኞች ጉዳት መጨመር ምክንያት ሆነዋል ተባለ

የአማዞን መጋዘን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አማዞን ኩባንያ በዕቃ ማከማቻው (መጋዘኑ) ውስጥ ተሰማርተው ያሉ ሮቦቶች ለሰራተኞች ጉዳት መጨመራቸውን አንድ የምርምር ጥናት ይፋ አድርጓል።

ዘ ሴንተር ፎር ኢንቨስቲጌቲቭ የተባለው ማእከል በባለፉት አራት አመታት ውስጥ 150 መጋዘኖችን ፈትሸና በርብሬ ነው ጥናቱን የሰራሁት ብሏል።

ጥናቱ ሮቦቶች ያላቸውና የሌላቸው መጋዘኖችንም አወዳድሮ ሮቦቶች ባላቸው የኩባንያው መጋዘኖች 50 በመቶ በሰራተኞች ላይ ክፉኛ ጉዳት አስከትለዋል ተብሏል።

አማዞን በበኩሉ ሪፖርት የተደረጉት ጉዳቶች ቁጥር ከፍተኛ የሆኑት ጥቃቅን የሚባሉ ጉዳቶችም በሰራተኞች ሲያጋጥሙ ሪፖርት እንዲያደርጉ ኩባንያው ስለሚያበረታታ ነው ብሏል።

ሪፖርቱን ያጠናቀረው ጋዜጠኛው ዊል ኢቫንስ ሲሆን በምርምር ማዕከሉም ድረ ገፅም ለህትመት በቅቷል።

ግዙፉ ኩባንያ አማዞን ያጋጠመውን የደህንነት ስጋቶችም ለመሸፈን ጥሯል በማለትም ወንጅሎታል።

የኩባንያው ኃላፊዎች ህዝቡንም ሆነ ህግ አውጭዎችን የሰራተኞች ደህንንትን ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ ሆን ብለው አሳስተዋል ብሏል።

ኩባንያው በበኩሉ ይህንን ፍፁም ውንጀላ ነው በማለት "ማንንም አላሳሳትንም፤ የሸፈንነውም ጉዳይ የለም" ብለዋል።

ጋዜጠኛው የሰበሰባው መረጃዎች በተቃራኒው የሚያሳዩት የሰራተኞቻችን ደህንነት ዋና ጉዳያችን እንደሆነ ነው ብለዋል።

አማዞን ሮቦቶችን በመጋዘኖቹ ማሰራት የጀመረው ከስምንት አመት በፊት ነበር።

የኩባንያው ሰራተኞች እንደሚናገሩት ሮቦቶቹ ከመጡ በኋላ ሰራተኞች በሰራ ቦታቸው ላይ ረዥም ሰዓት መቆም፣ አሰልቺና ተደጋጋሚ ስራዎችን መደጋጋም ይጠበቅባቸዋል።

ከዚያም በተጨማሪ ሮቦቶቹ በስራቸው ፈጣን በመሆናቸው የኩባንያው ሰራተኞችም ምርታቸውን ከአቅማቸው በላይ እንዲያፈጥኑት ይጠበቅባቸው ነበር።

ለምሳሌ በኩባንያው እቃ የሚያነሱ ሰራተኞች ከዚህ ቀደም 100 የነበረው በአራት መቶ እንዲያድግ ሆኗል።